አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 01 July 2017

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 የአፍሪካ ወጣቶችን በፖለቲካው መስክና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት በንቃት ለማሳተፍ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ የአፍሪካ ሕብረት ገለጸ።

አገሮች በተለይ ወጣት ሴቶችን ለአመራርነት የማብቃት ተግባር ማከናወን እንደሚገባቸው ነው ሕብረቱ ያሳሰበው።

በሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቴ ሴሶማ የወጣቶች ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ተሳትፎን በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የወጣቶች ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተሳትፎ በአገሮች ተጨባጭ ሁኔታ ቢለያይም እንደ አህጉር ሲታይ ግን ዝቅተኛ ነው።

በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች በፖለቲካ መስክ ለመሳተፍ የሚያስችላቸው ምቹና አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር አልተፈጠረላቸውም።  

በአሁጉሪቷ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እንዲቻል ወጣቶችን ማብቃትና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረግ እንደሚገባ ኮሚሽነር ሴሶማ ገልጸዋል።

ለዚህም አገሮች የወጣቶቻቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችሉ ሕጎችንና አዋጆችን በመቅረጽ መተግበር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

“በተለይ ወጣት ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ መገናኛ ብዙኃን፣ ምክር ቤቶችና ሲቪሉ ማኅበረሰብም ጭምር ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል” ብለዋል።

በሕብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ዳይሬክተር ዶክተር ካቤሌ ማትሎሳ በበኩላቸው፤ የወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት የአፍሪካ ዴሞክራሲያዊ ምርጫና አመራርነት ቻርተር እ.ኤ.አ በ2007 አጽድቀዋል።

ሆኖም አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ወጣቶችን በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት ላይ እንዲሳተፉ ከማድረግ አኳያ ክፍተቶች እንዳሉባቸው አመልክተዋል።

የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ለአጀንዳ 2063 ስኬታማነት ሲመክሩ የወጣቶችንም የፖለቲካ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ትኩረት ሰጥተው ሊወያዩበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውታል።

“ወጣቶችን ለፖለቲካ ማብቃት፣ ማበረታታት እና መደገፍ ለአገራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጭምር አቅም የሚፈጥር በመሆኑ አገሮቹ ለዚህ ትኩረት ሰጥተው ሊመክሩ ይገባል” ሲሉ ዶክተር ማትሎሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከጎልማሳው ኃይል ያነሰ ሲሆን፤ይህም የወጣቱ 65 በመቶ፣ የጎልማሳው ደግሞ 79 በመቶ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት በዚህ ዓመት ባሳተመው መጽሔት ገልጿል።

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳ ሶዶ 24/2009 የወላይታ ሶዶና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ከ5ሺህ 300 በላይ ተማሪዎችን  ዛሬ አስመረቁ፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በተከናወነው የምርቃ ስነስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰንበቴ ቶማ እንዳሉት ተቋሙ የዛሬዎቹን ጨምሮ ባለፉት 10 ዓመታት በመደበኛና በተከታታይ ፕሮግራሞች ከ25ሺ በላይ ተማሪዎችን አሰልጥኗል፡፡

ዩኒቨርስቲው ከመማር መስተማሩ በተጓዳኝ የአካባቢውን ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮች ላይ ትኩረት በማድረግ  እየሰራ ነው፡፡

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ሃገርንና ህዝብን በማስቀደም የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር እንዲሆኑም ዶክተር ሰንበቴ ጠይቀዋል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው ተመራቂዎቹ "ስራ ፈጣሪ በመሆን የበርካታ ወገኖችን የህይወት መንገድ ማመላከት ይኖርባቸዋል "ብለዋል፡፡

በድህነት ቅነሳ ዘርፍ  በሶስተኛው ዲግሪ የተመረቀው  ተክሌ ሌዛ የተለያዩ ምርምሮችን በማከናወን ለህብረተሰቡ ችግር ሳይንሳዊ የሆነ መፍትሄ በመስጠት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚጥር ተናግሯል፡፡

በኢንጅነሪንግ ትምህርት ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ የሆነችው ኤልሳቤት ቀናው በበኩሏ እያደገ የመጣውን የሃገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍየማገዝ ፍላጎቷ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ተመራቂዎቹ በመጀመሪያ በሁለተኛና  በሶስተኛ ዲግሪ  ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ለአራተኛ ጊዜ በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸው 1ሺህ 809 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡

ከተመራቂዎቹ ውስጥ 645 ሴቶች ናቸው፡፡                 

በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ ተማሪ ከበደ ጉርሜሳ "በትምህርት ዓለም አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚገጥሙ ቢሆንም ዓላማ ያለኝ በመሆኑ ዉጤታማ ሆኝያለሁ "ብልዋል፡፡

Displaying DSC_0681.JPG

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አብድልቃድር ሁሴን ተቋሙ ከተመሰረተ ወዲህ  ሶስት ሺህ 771 ተማሪዎችን  ማስመረቁን አመልክተው ወደፊትም አሁን ካለበት ደረጃ የትምህርት ክፍሎችን ከፍ በማድረግ በሃገርና በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን ትኩረት ስጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

Displaying DSC_0686.JPG

የዕለቱ የክቡር እንግዳ በትምህርት ሚኒስቴር የከፊተኛ ትምህርት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ከተማ መስቀላ ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ወደተግባር በመለወጥ ቤተሰባቸውና ሀገራቸውን  ማኩራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በ2004 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 የአፍሪካ ዕድገት በአጀንዳ 2063 እደርስበታለሁ ካለችው ዕቅድ አንጻር በትክክለኛ ጉዞ ላይ መሆኗ ተነገረ።

የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኮሚሽነር ዶክተር አንቶኒ ሞቴ በአጀንዳ 2063 ዕቅድ ዙሪያ ዛሬ በህብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በግማሽ ግፍለ ዘመን ይፈጸም ዘንድ የህብረቱ አባል አገራት ከአምስት ዓመት በፊት ያፀደቁት አህጉር አቀፉ ዕቅድ አፈጻጸም ሲታይ አፍሪካ በትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ላይ ትገኛለች ብለዋል ዶክተር አንቶኒ።

የአፍሪካዊያን የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪዎችና የከተሞች መስፋፋት አህጉሪቱ በኢኮኖሚው መስክ ስኬቶች ያስመዘገበችባቸው መስኮች ናቸው።

እ.አ.አ በ2004 ከነበረበት 14 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቷ በ2016 ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲያድግ 700 ግዙፍና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ አህጉሪቱ መጥተዋል።

ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለአህጉሪቱ መሰረተ ልማት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባለፈ የህብረቱ አባል አገራት ከዓመታዊ ምርታቸው ለዘርፉ የሚመድቡት ሃብት ከ10 ዓመት በፊት ከነበረበት 3 ነጥብ 5 በመቶ አሁን በዕጥፍ መጨመሩን ከህብረቱ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

አባል አገራቱ በዕቅዱ የተቀመጡ ነጻ የንግድ ቀጠና መመስረት፣ ከጥገኝነት የመላቀቅ አመለካከት መጨመር፣ በመሰረተ ልማት መተሳሰርና ዜጎችን ከድህነት ማውጣት ላይ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለለውጡ መመዝገብ ምክንያቶች መሆናቸውን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2016 በአህጉሪቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና ለግጭት ተጋላጭ የሆኑ አገራት በአማካኝ 6 ነጥብ 5 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያስመዘግቡ አጠቃላይ የአህጉሪቱ ዓመታዊ እድገት እስከ መጪዎቹ 5 ዓመታት ድረስ ከ6 በመቶ በላይ ይሆናል።

ኢኮኖሚያቸውን በተፈጥሮ ማዕድናትና ነዳጅ ላይ ያልመሰረቱ አገራት ጭምር ተከታታይ ዕድገት ማሳየታቸው በአዎንታዊነት ይታያልም ብለዋል።

"መስራት የሚችለው የሰው ኃይልና የከተሞች በፍጥነት መስፋፋት አፍሪካን ከሌሎች አህጉራት ባለ ተስፋይቷ አህጉር ያደርጋታል" ያሉት ዶክተር አንቶኒ ከ15 ዓመታት በኋላ በአፍሪካ መስራት የሚችለው የሰው ኃይል 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን እንደሚደርስ ተናግረዋል።

አሁን ባለው የአፍሪካ የከተሞች መስፋፋት በመጪዎቹ 10 ዓመታትም በከተማ የሚኖረው የህዝብ ብዛት ወደ 190 ሚሊዮን እንደሚያድግ ይጠበቃል።

ይሁንና የአገራቱ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ወደ ሌሎች አገራት አለመላክ፣ ለህዝብ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠት፣ የፈጠራ ቴክኖሎጂ አለመስፋፋትና የዴሞክራሲ ባህል አለመዳበር ለአህጉሪቱ ዕድገት ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶክተር አንቶኒ

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት የሰጠውን የእፎይታ ጊዜ መራዘም ተከትሎ 983 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ወደ አገራቸው ገብተዋል።

ከጂዳ 626 ፣ ከሪያድ ደግሞ 357 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውን የገለፀው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው።

ከሳዑዲ ዓረቢያ በተለይም ሪያድ ውስጥ ትኬት ገዝተው ለመመለስ ዝግጁ የሆኑ ዜጎችን ከሳዑዲ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ለመመለስ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ስምምነቱን ተከትሎም 290 ኢትዮጵያዊያን በሳዑዲ ዓረቢያ አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ እንዲጓጓዙ ተደርጓል።

በቀጣዮቹ ሁለት ቀናትም ከአየር መንገዱ ጋር በመቀናጀት ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል ሚኒስቴሩ።

በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በተደረገ ጥረት ባለፈው ሰኔ 20 ቀን 2009 ዓ.ም የተጠናቀቀው የእፎይታ ጊዜ ለአንድ ወር መራዘሙ ይታወቃል።

ዜጎች በተራዘመው የእፎይታ ጊዜ ሳይዘናጉ ወደ አገራቸው ለመመለስ ወደ ኢትዮጵያ ኢምባሲና ምዝገባ ጣቢያዎች በመሄድ የጉዞ ሰነድ እንዲወስዱ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ሕገ መንግስታዊ ልዩ ጥቅም የሚደነግገው ረቂቅ አዋጅ መንግስት ህዝባዊ ለመሆኑ መገለጫ መሆኑን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ገለጹ።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም እንደምታገኝ በደነገገው መሰረት የልዩ ጥቅም ድንጋጌ ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመራቱ ይታወቃል።

ኃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ረቂቅ አዋጁንና ከሳዑዲ ዓረቢያ ተመላሽ ዜጎችን አስመልክቶ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ሕገ መንግስቱ በስራ ላይ ከዋለ ከሃያ ዓመታት በኋላ በቅርቡ ይፋ የተደረገው ረቂቅ አዋጅ መውጣቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውና መንግስት ለህዝቡ ለሚሰጠው ክብር መገለጫ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሁሉንም ብሔርና ብሔረሰቦች በእኩል ዓይን የሚያስተናግድ ህዝባዊ መንግስት ለመሆኑ ማሳያ መሆኑንም ነው የገለጹት ዶክተር ነገሪ።

አዋጁ "በታሪክ አጋጣሚ የተከሰቱ የታሪክ መዛባትን እያነሳን ወደኋላ የምናስብበት ሳይሆን ወደ ፊት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት እንድናደርግ የሚያግዝ" ነው በማለት ገልጸዋል።

በሕገ መንግስቱ ላይ የተጠቀሰው የልዩ ጥቅም አዋጁ እስካሁን እንዴት እንደዘገየ ጥናት ተደርጎ ሳይሳዊ ምክንያት እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዶክተር ነገሪ፤ በአሁኑ ወቅት እንዲወጣ የገፋፋው "ልዩ ምክንያት ኖሮ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

"አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረትና ለበርካታ ዓለምአቀፍ ተቋማት ማዕከል በመሆኗ የኦሮሞ ህዝብ በተለይም አዲስ አበባ በተከተመችበት አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ለከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለዓለም ያበረከቷት ስጦታ ናት" ብለዋል።

ልዩ ጥቅሙም በታሪክ አጋጣሚ ለተፈጠሩ ለሁሉም የኦሮሞ ህዝብ ጉዳት ካሳ ለመስጠት ሳይሆን የነበረውን ታሪክ በማስተካከል ለህዝብ ክብርና ጥቅም ሲባል የተደረገና በአንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የተሻለች አገር ለመገንባት ያለመ መሆኑን ነው ያብራሩት።

ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ውክልና የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኦሮሚያ ክልልና የፌደራል መንግስት አመራሮችና የህግ ተቋማት የተወያዩበት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ነገሪ፤ ህዝብ ሳይወያይበት ለተወካዮች ምክር ቤት እንዴት እንደተመራ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ህዝቡ በቀጣይ እንደሚወያይበት ምላሽ ሰጥተዋል።

የረቂቅ አዋጁ ይዘት የሌሎችን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መብቶችና ጥቅሞች በምንም መልኩ የማይሸራርፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

ልዩ ጥቅሞች በአብዛኛው ግለሰባዊ ሳይሆኑ ተቋማዊ በመሆናቸው የከተማዋና የክልሉ ሕዝቦች ትስስርና መስተጋብር ይበልጥ ሕጋዊ መስመር ይዞ እንዲጠናከር የሚያደርግና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት እንደሚሆን ነው ያብራሩት።

ልዩ ጥቅሙን በተዛባ መልኩ በማየት በህዝቦች መካከል መቃቃርን ለመፍጠርና የአብሮነት እሴታቸውን ለመሸርሸር የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የረቂቅ አዋጁ ይዘት የአዲስ አበባን ወሰን አለመግለጹ ወደፊት በከተማ አስተዳደሩና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሚቋቋመው የጋራ ምክር ቤት እንደሚወሰንና አሁንም ከአዋጁ ውጭ በክልሉና በከተማ አስተዳደሩ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን አንስተዋል።

በሌላ ዜና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎችን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ዙሪያ ኃላፊ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ዜጎች ከአገሪቱ እንዲወጡ የሰጠው የሶስት ወራት የእፎይታ ጊዜ ቢጠናቀቅም ግማሽ ያህሉን ማስመለስ ባለመቻሉ መንግስት ባከናወናቸው የዲፕሎማሲ ተግባራት ሳዑዲ ተጨማሪ 30 ቀናት መፍቀዷን ገልጸዋል።

እስካሁንም ለመመለስ ፓስፖርት ከወሰዱ ከ111 ሺህ ዜጎች መካከል 50 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችን ማስመለስ መቻሉን ነው የተናገሩት።

ከሰኔ 18 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ተጨማሪ ቀናት ቢሰጡም ዜጎች ሳይዘናጉ በወቅቱ እንዲመለሱ ዶክተር ነገሪ ጥሪ አቅርበዋል።

"መንግስትም ተመላሽ ዜጎችን ለማቋቋም አዲስ አበባን ጨምሮ ከክልል መንግስታት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ ነው" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 ተመራቂዎች የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ችግሮች የመፍታት ድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር አስገነዘበ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 40 ተማሪዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስመርቋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል 259 በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 781 ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ ዘርፎች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር ታገሰ ጫፎ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ተመራቂዎች የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ችግሮች በየደረጃው ለመፍታት የሚጠበቅባቸውን መስዋዕትነት መክፈል ይጠበቅባቸዋል።

የአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ አመለካከት በመያዝም የህዝቡን ፍላጎት በሚገባ የሚያሟሉና ከሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን የፀዱ መሆን እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።  

በዚህም መልካም አስተዳደርን ማስፈን የሚችል ሲቪል ሰርቫንት እንዲኖር ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይ ለታዳጊ ክልሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች በመስራት የሰው ኃይል በማብቃት ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ከአገሪቱ የለውጥ እርምጃዎች ጋር የሚጣጣሙ ተግባራትን ይበልጥ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በፌዴራልና በክልል መንግስታት መስሪያ ቤቶች የሚያገለግሉ ባለሙያዎችን ብቃት የማሳደግ ስራ እያከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው ምሩቃኑ በቆይታቸው ያካበቱትን ዕውቀትና ክህሎት ለአገራዊ ለውጥና ለሕዝብ አገልግሎት በማዋል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በፍላጎት ላይ የተመሰረቱ አጫጭርና ተከታተይ ስልጠናዎችን በመስጠት የመንግስት ሰራተኛውን የእውቀት፣ የክህሎትና የአመለካከት ክፍተቶች ለመሙላት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአገሪቱ የሚካሔደውን የአቅም ግንባታና የሪፎርም ፕሮግራሞች ትግበራ ለማሳካት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

የጥናትና ምርምር አገልግሎትን ለማሳደግ ከሚያካሂዳቸው 39 የጥናትና ምርምር ስራዎች በተጨማሪ ከተለያዩ የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማት ጋር በመተባበር አገራዊና ሴክተር ተኮር ፕሮጀክቶችን እየከወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፐብሊክ ሰርቪሱን ችግሮች የበለጠ ለመገንዘብ የመፍቻ ስልቶችን በመለየትና በችግሮቹ ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የማማከር አገልግሎት በመስጠት፤ የመንግስት ተቋማት አሰራርና አደረጃጀት እንዲሻሻል ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና የመልካም አስተዳደር መርሆዎች በፐብሊክ ሰርቪሱ እንዲሰርጹ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተም ይገኛል።

ከ22 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዛሬዎቹን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 ሁሉም አፍሪካዊ ህፃን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2020 ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄድ ለማድረግ እንደሚሰራ የአፍሪካ ሕብረት አስታወቀ።

ሕብረቱን ከሌሎች የፋይናንስ ምንጮች ተፅእኖ ለማውጣትም እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

የሕብረቱ ምክትል ሊቀመንበር ቶማስ ክዌሲ ኳርቴይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት መጪዋ አፍሪካ የተማሩና አምራች ዜጎች ያሉባት ተጽዕኖ ፈጣሪ ትሆናለች።

እርሳቸው እንደሚሉት በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች የሚኖሩባት አፍሪካ ከሃያ ዓመት በኋላ የወጣቶቿ ቁጥር በእጥፍ ያድጋል፤ ከተማሩና አምራች ከሆኑ ደግሞ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚ ይኖራታል።

ወደ አውሮፓ ለመግባት በበረሃና በውሃ ላይ አሰቃቂ ጉዞ የሚያደርጉትን ያስታወሱት ምክትል ሊቀመንበሩ የተማሩ ወጣቶች እንዳልተማሩት በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደማይሰደዱ ነው የተናገሩት።

ሚስተር ቶማስ ኳርቴይ፤ አንዳንድ የሕብረቱ የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎች ድጋፋቸውን እንዳቋረጡ አስታውሰው የሕብረቱን የገንዘብ ምንጭ በአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና መርሃ ግብር 75 በመቶውን ለመሸፈን መሪዎቹ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

እስካሁን በአባል አገራቱ በኩል ሕብረቱን በገንዘብ ለመደገፍ የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ነጻ የንግድ ቀጣናዎችን በመሳሰሉ ፕሮግራሞች ቀሪውን የፋይናንስ ፍላጎት እንደሚያሟሉ ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2009 የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ የትምህርት ዘርፎችን ሊከፍት ነው።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 475 ተማሪዎች ከንቲባ ድሪባ ኩማ እና ሌሎች ከፍተኛ የመዲናዋ  አመራሮች በተገኙበት ዛሬ አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብረሃነመስቀል ጠና በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት የከተማዋን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ ፕሮግራሞችን  በሚቀጥለው ዓመት ለመጀመር የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ከሚከፈቱ የትምህርት ዘርፎች መካከል ኮኦፕሬቲቭ ማኔጅመንት፣ የከተማ ስነ-ህንጻ ቴክኖሎጂ፣ የከተማ ግብርና፣ የሶሻል ወርክ ትምህርትና የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ይገኙበታል።

የትምህርት ዘርፎቹ በመዲናዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚፈቱና ከወደፊት እድገቷ ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው ብለዋል ዶክተር ብረሃነመስቀል።

ዩኒቨርሲቲው ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 950 በዲግሪ፣ 980 በዲፕሎማና ቀሪዎቹ ደግሞ በሰርተፊኬት ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል የሴቶች ቁጥር ከግማሽ በመቶ በላይ መሆኑ ዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ከንቲባ ደሪባ ኩማ በበኩላቸው አገሪቱ የያዘችውን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ የመሰለፍ ራዕይ ለማሳካት ተመራቂ ተማሪዎች እውቀታቸውን በመጠቀምና መልካም ስነ-ምግባርን በመላበስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የዛሬው የኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ በ1951 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ኮሌጅ በሚል ስያሜ የተመሰረተ ሲሆን የዘንድሮዎቹን ጨምሮ እስካሁን ከ65 ሺህ የሚበልጡ ሰልጣኞችን አስመርቋል። 

Published in ማህበራዊ

ደብረማርቆስ ወልዲያ ሰኔ 24/2009 የደብረ ማርቆስና የወልዲያ ዩኒቨርስቲዎች በተለያየ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን 6 ሺህ ተማሪዎች ዛሬ አስመረቁ።

ከተመራቂዎቹ መካከል የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በመደበኛ፣ በማታውና በክረምቱ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ሦስት ሺህ 500 ተማሪዎች ናቸው፡፡

ዩንቨርስቲው ፕሬዘዳንት ዶክተር ንጉሴ ምትኩ  ከተመራቂዎቹ ውስጥ  ከአንድ ሺህ በላይ ሴቶች ሲሆኑ 250  ደግሞ በድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን የተከታተሉና ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ለ9ኛ ጊዜ ተማሪዎችን ያስመረቀው የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የእለቱ ተመራቂዎችን ጨምሮ ከ28ሺ በላይ ተማሪዎችን አስተምሯል፤ አሁንም ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

የፌደራል መንግስት የፋይናስ ተቋማት ዋና ዳሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደ ሚካኤል  ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት  በመጠቀም ለሃገራቸውና ለህዝባቸው እድገትና ብልፅግና ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በማዕረግ የተመረቀው ዋለልኝ አብይ "ለወደፊት በትምህርቱ ውጤታማ እንደሆንኩት ሁሉ ስራ ጠባቂ ሳልሆን  ስራ ፈጣሪ በመሆን እራሴንና ሀገሬን ለማሳደግ እሰራለሁ" ብሏል።

ከግብርና ትምህርት ክፍል በሴቶች የዋንጫ ተሸላሚዋ  አሳየች አግደው በበኩሏ ለአካባቢ ተስማሚ፣  የመሬትን ለምነት የሚያዳብሩና የላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን እጽዋቶች በማላመድ ማህበረሰቡ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አግባብ ተግባራዊ የማድረግ እቅድ እንዳላት ተናግራለች።

በሌላ በኩል የወልዲያ ዩኒቨርስቲ ለአራተኛ ጊዜ በዲግሪ ፕሮግራም ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ  500 ተማሪዎችን አስመርቋል።

ዩኒቨርስቲው ያስመረቃቸው ተማሪዎች በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ ፕሮግራም የሰለጠኑ ሲሆኑ ከተመራቂዎች ውስጥም 828  ሴቶች ናቸው፡፡

ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀ " ሀገራችን  በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ብቁ የሆነ የሰው ሃይል ማፍራት የማይተካ ድርሻ አለው " ብለዋል።

መማር የሚጠቅመው በተግባር ሲውል በመሆኑ ምሩቃኑ እውቀታቸውን በተግባር እንዲያሳዩም አሳስበዋል፡፡

"ድህነትን ድል ማድረግ የሚቻለው የምሁራን ሁለገብ አስተዋጽኦ ሲኖር ነው "ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተርና የዩኒቨርስቲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።

ምሩቃን በግልና በቡድን እየሆኑ የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩና መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከጎናቸው እንደማይለይ ገልፀዋል።

ወልዲያ ዩኒቨርስቲ በዚሁ ወቅት ከ14ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይእንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡

በዩኒቨርስቲዎቹ የምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Published in ማህበራዊ

አምቦ ጅማ ሰኔ 24/2009 የአምቦና የጅማ ዩኒቨርስቲዎች ከ6 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቁ።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት አቶ ታደሰ ቀነአ በምርቃው ሥነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብር ካስመረቃቸው መካከል 1 ሺህ 258 ሴቶች ናቸው።

ተመራቂዎቹ ከተከታተሏቸው የትምህርት መስኮች መካከል ኢንጂነሪንግ ፣ ሕግ እንዲሁም ጤና ሳይንስ ፣የተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ይገኙበታል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤና   የአምቦ ዩኒቨርስቲ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባ ዱላ ገመዳ በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት አበርክተዋል።

አቶ አባ ዱላ ሽልማቱን ከሰጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር "የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ይህ የመጨረሻ ግባችሁ  እንዳልሆነ አውቃችሁ በምትሰማሩበት ሙያ  ለሀገራቸው እድገትና ብልጽግና መትጋት ይጠበቅባችኋል" ብለዋል።

በእርሻው የትምህርት  ዘርፍ የተመረቀው  ሌመኔ ተመሰገን በሰጠው አስተያየት በተማረበት ሙያ የራሱን ሥራ በመፍጠር ለመስራት መዘጋጀቱን ተናግራል።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ  በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች ከ23 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ከዩኒቨርስቲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በተያያዘ ዜና የጅማ ዩኒቨርሰቲ 2 ሺህ 500 ተማሪዎችን ሲያስመርቅ የዩኒቨርስቲው ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ  እንዳስታወቁት ከተመራቂዎቹ መካከል 136  የህክምና ዶክተሮችና 425 ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ የሰለጠኑ ይገኙበታል፡፡

ማህበራዊና ጤና ሣይንስ፣ሥነ-ባህሪ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ተመራቂዎቹ ከሰለጠኑበት የትምህር መስኮች መካከል የተጠቀሱ ናቸው።

በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት የሰጡት በምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ኢንዲስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊና የዩኒቨርስቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ