አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በግማሽ ዓመቱ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ አገበያይቷል

399 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ቢሊዮን በላይ ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ማገበያየቱን ገለጸ።

በምርት ገበያው የፕላንና ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዋና ኦፊስር አቶ አብነት በቀለ በበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ምርት ገበያው በግማሽ ዓመቱ 275 ሺህ 770 ቶን ምርት ወይም 10 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለማገበያየት ማቀዱን አቶ አብነት ገልጸዋል።

በዚህም 317 ሺህ 607 ቶን ምርት በ14 ነጥብ 47 ቢሊዮን ብር በማገበያየት ከእቅዱ በላይ በመጠን 23 በመቶ በዋጋ 42 በመቶ አገበያይቷል ብለዋል።

በስድስት ወሩ 133 ሺህ 818 ቶን ቡና በዘጠኝ ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን ከተገበያየው ቡና ውስጥ 82 በመቶ የወጪ ቡና ምርት መሆኑን ጠቁመዋል።

በምርት ገበያው የተገበያየው ቡና በዕቅድ ከተያዘው የ17 በመቶ ብልጫ ያለው ከመሆኑም በላይ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ22 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

ከቡና በመቀጠል በምርት ገበያው በከፍተኛ መጠን የተገበያየው ምርት ሰሊጥ ሲሆን 5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር  ዋጋ ያለው 166ሺህ 691 ቶን ሰሊጥ ግብይት መፈጸሙን ተናግረዋል።

ከቡናና ሰሊጥ ግብይት ባሻገር ከ16 ሺህ ቶን በላይ ነጭ ቦለቄ፣ 227 ቶን አረንጓዴ ማሾና 87 ቶን ቀይ ቦለቄ ግብይት ተከናውኗል።

በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ ተከታታይ እርምጃዎች በመወሰዳቸውና የግብይት መድረኩ ፍትሐዊ መሆኑ ለምርት ገበያው አፈጻጸም መሻሻል  ምክንያቶች መሆናቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

ባለፉት ስድስት ወራት 79 የግብይት ህግ ጥሰቶች የተፈጸሙ ሲሆን ድርጊቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ መቀነሱም ተገልጿል።

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን