አርዕስተ ዜና

በሽራሮ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ለማከናወን እንቅስቃሴ ተጀመረ

387 times

ሽሬ እንዳስላሴ የካቲት6 /2010 የህዳሴው ችቦ ሸራሮ ከተማ መግባቱን ተከትሎ በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ ለማከናወን  እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ ።

የህዳሴው ችቦው ትናንት ሸራሮ ከተማ ሲገባ የዞኑ ህዝብ ደማቅ አቀባበል አደርጓል።

 የሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን ችቦውን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የአንድነታችን መሰረት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተባበረ ክንዳችን እውን ይሆናል።

የዞኑ ህዝብ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ30 ሚሊዮን 700ሺህ  ብር በላይ በስጦታና በቦንድ ግዥ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ችቦው ወደ ዞኑ  መግባቱን ተከትሎ በአካባቢው እየተዘዋወረ  በሚቆዩባቸው አራት ቀናት ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ለመፈፀም ታቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን አቶ ተክላይ አስታውቀዋል፡፡

የህዳሴ ችቦውን ለመቀበል ወደ ሸራሮ ከተማ አደባባይ ወጥተው ከተቀበሉት መካከል መምህርት መሰረት አሰፋ በሰጡት አስተያየት የህዳሴ ችቦ  አቀባበል ምክንያት በማድረግ የሦስት ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲልም ለሦስት ተከታታይ ዙሮች የዘጠኝ ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን የተናገሩት አስተያየት ሰጪዋ፣የግድቡን ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ አቶ አብርሃለይ ታረቀ በበኩላቸው ከአሁን ቀደም  የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን አሁን የዳሴው ችቦ ወደ አካባቢው መምጣቱን ተከትሎም የአራት ሺህ ብር ቦንድ ግዥ መፈጸማቸውን አመልከተዋል።

የህዳሴ ግድብ እውን ሆኖ የኤለክትሪክ ሃይል እስኪያመነጭ ድረስ አቅማቸው  የፈቀደውን ሁሉ ለማበርከት መዘጋጀታቸውንም ጨምረው  አስታውቀዋል ።

የሸራሮ ከተማ ነዋሪ ወጣት ኪዳኔ ተስፋይ በዚሁ ወቅት እንዳስታወቀው ታላቅ ክብር  የሆነው የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት የሚጀምርበትን ቀን በታላቅ ጉጉት እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል።

Last modified on Wednesday, 14 February 2018 00:31
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን