አርዕስተ ዜና

የግብርና ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል ምርጫ ሳይሆን ወሳኝ ተግባር ነው ---ዶክተር ኢያሱ አብርሃ

408 times

አዳማ የካቲት 6/2010 የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ግቦች ለማሳካት የመስኖ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል ወሳኝ ተግባር መሆኑን  የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ  ዶክተር ኢያሱ አብርሃ ገለጹ።

ሚኒስትሩ እንዳሉት  የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ሁለተኛው ዙር እቅድ በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ፈጣንና መሰረተ ሰፊ እድገት በማስቀጠል የመወዳደር አቅምን  ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ።

እቅዱ ምርታማነት ፣ ጥራትና ተወዳዳሪነት በላቀ ደረጃ በማሳደግ በሀገሪቱ የተጀመረውን የትራንስፎርሜሽንና የህዳሴ ጉዞ  በማፋጠን በ2017 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።

"በእቅዱ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ደግሞ ለግብርና ስራ የመሰኖ ውሃ አቅርቦትን ማሻሻል ምርጫ ሳይሆን ወሳኝ ተግባር ነው " ብለዋል ዶክተር ኢያሱ።

"መንግስት የመስኖ ልማት ዋና አጀንዳው በማድረግ ውሃን ማዕከል ያደረገ የግብርና ልማት መከተል ከጀመረ ውሎ አድሯል "ያሉት ሚኒስትሩ የመስኖ  መሰረተ ልማቶችን ለማስፋፋት በየደረጃው የሚታዩ የአቅም ክፍተቶችን በመሙላት የመፈፀም አቅማችንን ማሳደግ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ዘርፉን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበርን እንዲያፋጥኑ  ከተዘጋጁ ምሰሶ ፕሮግራሞች መካከል አንዱ  የግብርና እድገት ፕሮግራም የመጀመሪያ ምዕራፍ በስኬት አጠናቆ ወደ ቀጣዩ ለመሸጋገር ርብርብ እየተደረገ መሆኑ የተናገሩት ደግሞ የፕሮግራሙ ብሄራዊ አስተባባሪ አቶ ከበሩ በላይነህ ናቸው ።

የግብርና እድገት ፕሮግራም በመጀመሪያው ምዕራፍ 280 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት በማሰባሰብ 18 ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ አውታሮች ለመገንባት ታቅዶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በዚህም 327 ሚሊዮን ዶላር በማሰባሰብ እና 41 ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ አውታሮች በመገንባት በስኬት መጠናቀቁን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

በተከናወነው ስራም  በ4 ክልሎችና በ96 ወረዳዎች የሚገኙ  3 ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶና አርብቶ አደሮች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልፀዋል ።

በፕሮግራሙ ሁለተኛ ምዕራፍ ወደ ሰባት ክልሎች ፣ አንድ  የከተማ አስተዳደርና 165 ወረዳዎች በማስፋት 10 ሚሊዮን አባወራዎች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ለማስፈጸሚያም 581 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሀብት በማሰባሰብ 55 ሺህ ሔክታር መሬት የሚያለሙ የመስኖ  አውታሮች በመገንባት ላይ እንደሚገኝ  አቶ ከበሩ ተናግረዋል።

"ፕሮግራሙ የመስኖ አውታሮች መገንባት ብቻ ሳይሆን የተገነቡት ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ፣ የተመረተው የሚከማችበትና ለገበያ የሚቀርብበት የባለሙያ እገዛ ጭምር የማመቻቸት ስራ ያካተተ ነው" ብለዋል ።

ዘርፉ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ሴቶችና ወጣቶች ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ሲሆን የኤክስቴንሽን አገልግሎት ለሚሰጡ አካላትም የመኪና ፣ የሞተር ብስክሌትና የብስክሌት አቅርቦት እየተሟላ ነው ተብሏል ።

በአነስተኛ መስኖ ልማት የዲዛይንና ግንባታ ዙሪያ በአፈፃፀም ወቅት የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ቀጣይ የትግበራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በአዳማ ከተማ  የምክክር መድረክ  ተካሄዷል።

በፕሮግራሙ አፈፃፀም ሂደት የሚታዩ የመስኖ ልማት አውታሮችን በጊዜና በጥራት አጠናቅቆ ያለማቅረብ ችግር ለመፍታት በመድረኩ የግንባታ ተቋራጮች ማህበርና የአማካሪ መሀንዲሶች ተወካዮች የመወያያ ፅሁፍ አቅርበዋል ።

ለግንባታው መጓተት  የአቅም ውሱንነት ፣ የጨረታ መጓተት፣ የፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ክፍተቶች በዋነኛነት ተነስተዋል ።

ለአንድ ቀን በተካሄደው በዚሁ መድረክ  በዘርፉ የሚሰሩ የክልልና የዞን አመራሮች ፣ የውሃ ስራዎች ተቋራጮችና የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን