አርዕስተ ዜና

የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

434 times

አዲስ አበባ የካቲት 5/2010 የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ ከየካቲት 12-16 /2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት 16ኛውን የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ጉባኤ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ጉባኤው "የመንገድ ሃብታችንን በመንከባከብ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንረባረብ" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ረሺድ መሐመድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የ35 የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ከ200 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል።

ይህም በአገሪቷ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት፣ ለአገር ገጽታ ግንባታና በመንገድ ዘርፍ ግንባታ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ምርጥ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ያስችላል ብለዋል።

ጉባዔው ባለፈው ዓመት በኮትዲቯር ዋና ከተማ አቢጃን የተካሄደው 15ኛው ጉባዔ ውሳኔዎች አፈጻጸምን የሚገመግም ሲሆን የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል።

ኢትዮጵያ ማኅበሩን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ እየመራች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ረሺድ በጉባዔው ማኅበሩን ለቀጣይ ሁለት ዓመት የሚመራ ፕሬዝዳንት ምርጫ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ከአዲስ አበባ አዳማ የባቡር ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን ስለ አገሪቱ የባቡር ኢንዱስትሪ ገለጻ ይደረግላቸዋል፤ የአዲስ-አዳማን የፍጥነት መንገድም ይጎበኛሉ።

የአፍሪካ የመንገዶች ጥገና ፈንድ ማህበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 የተቋቋመ ሲሆን በአባል አገራት የሚገኙ መንገዶችን ለመጠገን፣ ለመጠበቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚሰራ ተቋም ነው። 

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት 35 የአፍሪካ አገራትን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን