አርዕስተ ዜና

ባህርዳር ከተማ ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ባለቤት ሆነች

522 times

ባህርዳር የካቲት 4/2010 ባህርዳር በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪ ሆና እንድትዘልቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

በከተማዋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ የመሰረተ ልማት አውታሮች ዛሬ ተመርቀዋል።

ርዕሰ-መስተዳደሩ በምረቃው ወቅት እንዳስታወቁት ባህርዳር ካላት የተፈጥሮ ጸጋ ባለፈ በኢንዱስትሪ በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ክልሉ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።

"ባህር ዳር የልማት ከተማ ናት" ያሉት አቶ ገዱ መንግስት የመሰረተ ልማቷን ለማሟላት የሚያደርገውን ጥረት ህብረተሰቡ እንዲደግፍና የተሰሩትንም በባለቤትነት በመጠበቅ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በቀጣይም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በመፍታት የመፍትሄው አካል እንዲሆን እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ አየነው በላይ በበኩላቸው በህብረተሰቡ የሚነሱ የልማት ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ ባለፉት ሦስት ዓመታት 10 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ 16 ኪሎ ሜትር የጥርብ ድንጋይ መንገድ ግንባታ ለማከናወን ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም 40 ኪሎ ሜትር ጠጠር መንገድና 30 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ በመገንባት አጠቃላይ የከተማዋን የመንገድ ርዝመት 667 ኪሎ ሜትር በማድረስ ሽፋኑን 63 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልፀዋል።

የ11 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዳር መብራት፣የእግረኛ መንገድ ግንባታ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ስራና የአረንጓዴ ልማት ፓርኮች ግንባታ  መከናወኑንም ተናግረዋል።

በመሰረተ ልማት ግንባታዎች የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተከናወኑት የልማት ስራዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ከንቲባው አስረድተዋል።

በዚህ ዓመትም ከገጠር መንገድ እስከ አውሮፕላን ማረፊያ የ 4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ ማስፋፊያ፣የ12 ኪሎ ሜትር የጥርብ ድንጋይ መንገድ፣ 10 ኪሎሜትር የፍሳሽ ማስወገጃና መሰል ስራዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማው ነዋሪ አቶ አያሌው አስፋው ባህርዳር ከተማ ለብዙ ጊዜ በመሰረተ ልማት ተረስታ የኖረች እንደነበረች አስታውሰው፤ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ እየተከናወነ ያለው የልማት ስራ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።

አዳዲስ መንገዶችን በመክፈት፣ ጨለማ ወርሷቸው የነበሩ አካባቢዎችን የመብራት መስመር በመዘርጋት፣ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር በመቻሉም የከተማዋ ዘመናዊነት እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

"በየአካባቢው የሚገነቡ የመንገድ መሰረት ልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ከጭቃና ከአቧራ ከማላቀቃቸውም በላይ መንገዶችን ተከትሎ የመኖሪያ አካባቢዎች ሱቅ በመክፈት የገቢ ምንጭ እየሆኑ ነው" ያለችው ደግሞ ወጣት ጥሩዘር ታከለ ናት።

እነዚህ የልማት ስራዎች የከተማዋን እድገት ከማፋጠናቸውም በላይ የወጣቱን ተስፋ ያሳደጉና ለስራ እድል ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን ገልጻለች።

ከተመረቁት የመሰረተ ልማቶች ማካከልም ከዲፖ ሆስፒታል እስከ የተባባሩት ማደያ የተገነባውን የአስፓልት መንገድ ጨምሮ በየክፍለ ከተማው የተገነቡ የጥርብ ድንጋይ መንገድና ሌሎችም ይገኙበታል።

በመሰረተ ልማቱ ምረቃ ላይ የከተማዋ ነዋሪዎችና የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን ለግንባታዎቹ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም እውቅና ተሰጥቷል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን