አርዕስተ ዜና

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አራት የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ሥራ ለመጀመር እየተዘጋጁ ነው

607 times

ደሴ የካቲት 4/2010 በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ አራት የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች ሥራ ለመጀመር የማሽን ተከላ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ፓርኩ አስታወቀ፡፡

የፓርኩ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዝመራው ደጀን እንዳስታወቁት በኢንዱስትሪ ፓርኩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኢንዱስትሪዎች በመሰማራት ላይ ይገኛሉ።

አስካሁንም የደቡብ ኮሪያ፣ የቻይና፣ የጣሊያንና የአሜሪካ ኩባንያዎች ፓርኩ ውስጥ ስራ ለመጀመር ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ የማሽን ተከላና ማሽነሪዎችን የማጓጓዝ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የደቡብ ኮሪያው ፑንግ ኩክ ኩባንያ በቦርሳ፣ የቻይናው ሳይቴክስ በጨርቃጨርቅ ክሮች፣ የአሜሪካው ትራይባስ በወንዶች ሙሉ ልብስ፣ የጣሊያኑ ካርቪኮ በስፖርት ትጥቆች ምርት ተሰማርተው ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ መሆናቸውን አቶ አዝመራው ተናግረዋል፡፡

" የኩባንያዎቹ ሥራ መጀመር በአካባቢው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴን ከማጠናከር ባለፈ በአገር ውስጥ የሚገኙ መሰል ፋብሪካዎች የተሻለ ልምድ በመቅሰም የተወዳዳሪነት አቅማቸው እንዲጎለብት እድል ይፈጥርላቸዋል" ብለዋል፡፡

ኩባንያዎቹ የማሽን ተከላ ሥራቸውን እንዳጠናቀቁ በዚህ ዓመት ሥራ ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ያመለከቱት አቶ አዝመራው፣ አራቱ ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው ወደሥራ ሲገቡ በሁለት ፈረቃ ለ20 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ የተገነቡት ሼዶች ሙሉ በሙሉ ተከራይተው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአውሮፕላን ማረፊያና ለባቡር ትራንስፖርት ቅርብ መሆኑ፤ በወደብ አቅራቢያ የሚገኝና አስተማማኝ የከርሰ ምድር ውሃ የሚገኝበት መሆኑ ለኩባንያዎቹ አፈጻጸም ውጤታማነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስተባባሪው ጠቁመዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አህመዲን መሐመድ በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲው በጨርቃጨርቅ ትምህርት ክፍል በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

"የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሥራ መጀመር ለዩኒቨርሲቲው እንደ ቤተሙከራ ስለሚያገለግል ብቁ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ያግዘናል" ብለዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ጋሻው ጥላዬ በበኩላቸው "የኢንዱስትሪ ፓርኩ መገንባት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል" ብለዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን ለቴክኖሎጂና ለእውቀት ሽግግር ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ የከተማዋን እድገት እንደሚያፋጥን አስረድተዋል፡፡

የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ90 ሚሊዮን ዶላር በሚልቅ ወጭ ተገንብቶ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መመረቁ ይታወሳል ።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን