አርዕስተ ዜና

በአገሪቷ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ማስፋፋት ይገባል Featured

15 Apr 2016
1169 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 7/2008 በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን በሁሉም አካባቢ ተደራሽ ማድረግ አስተማማኝ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር ያግዛል።

እነዚህን አገልግሎቶች ማስፋፋት የቁጠባ ባህልን ለማሳደግና ገንዘብን በሚፈለገው ቦታና ጊዜ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተገልጿል።

ይህ የተባለው ዛሬ በአገሪቷ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የገንዘብ ዝውውር ወይም የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አስመልክቶ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የገንዘብ አገልግሎት ሥልጠናና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ወልዳይ አማሃ በዚህ ወቅት እንደገለፁት አብላጫው የአገሪቷ ነዋሪ ገንዘቡን የሚያንቀሳቅሰው የፋይናንስ ተቋማትን ሳይጠቀም በመሆኑ የቁጠባ ባህሉ ዝቅተኛ እንዲሆንና ተጨማሪ ሃብት እንዳያፈራ አድርጓል።

የባንክ አገልግሎት የማይጠቀሙ ሰዎች ቁጥር በርካታ መሆኑንና አገልግሎቱም በዚያኑ ያህል ተደራሽ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ባንክ አገልግሎቶች ጊዜንና ጉልበትን ለመቆጠብና የባንክ አገልግሎቱን ለማዘመን ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም የተናገሩት ዶክተር ወልዳይ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች መስፋፋት የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በአገሪቷ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች በቅርብ ጊዜ መጀመራቸውንና አገልግሎቱን በየወረዳው ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ወልዳይ ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነር የተባለ ተቋም ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነቢል ቀሎ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶች ማስፋፋት ባንኮችን እርስ በእርሳቸው በማገናኘት ለተገልጋዩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ጊዜንና ጉልበትን ለመቆጠብ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀም ጤናማ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ ህብረተሰቡ በሚፈልገው ሰዓትና  ቦታ ላይ ገንዘብ ለመጠቀም ያስችለዋል ነው ያሉት።

አገልግሎቱን መሰረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ጭምር በቀላሉ ማዳረስ የሚቻል መሆኑን የገለፁት አቶ ነቢል አገልግሎቱ ገንዘብን በጥሬው መያዝ የሚያስከትለውን አደጋ እንደሚቀንስም ገልጸዋል።

እነዚህ አገልግሎቶች ባንኮች በሚያወጡት ህግና መመሪያ መሰረት የሚከናወኑ ሲሆን የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውንም ዓይነት ክፍያ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን በመጠቀም ማከናወን ገንዘብን ለመቆጠብና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠቀም እንደሚያስችልም አስታውቀዋል።

የሞባይል ገንዘብ ማስተላለፍ አማካሪ የሆኑት ኢናሲዮ ማስ በበኩላቸው ማንኛውም ሰው የሞባይል ወይም የኢንተርኔት አገልግሎቶችን በመጠቀም ገንዘቡን በአስተማማኝ መንገድ መጠቀምና ማስተላለፈ የሚችል በመሆኑ አገልግሎቱን ማስፋፋት ለአገሪቷ የፋይናንስ ዕድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።

በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ማንኛውም ሰው የባንክ ደብተር ሳያወጣ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ጨምሮ ከተለያዩ ገንዘብ አስተላላፊ ኤጀንቶች አገልግሎቱን ማግኘት ይቻላል።

ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ደንበኞች ባሉበት አካባቢ የሞባይል ስልካቸውን፣ ኢንተርኔት ወይም ኤቲ ኤም ካርዳቸውን በመጠቀም በቀላሉ ገንዘብ እንዲልኩና እንዲቀበሉ፣ ገንዘብ ተቀማጭ ወይም ገቢ እንዲያደርጉ፣ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ነው።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ