አርዕስተ ዜና

በሰሜን ሸዋ በበጋው መስኖ ከለማው መሬት አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰበሰበ

229 times

ደብረ በርሃን 8/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን በበጋው ወቅት በመስኖ ከለማው መሬት አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡ ተገለጸ፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ መስኖ ውሃ አጠቃቀም ቡድን መሪ ወይዘሮ አስካለ ይፍሩ ለኢዜአ እንዳሉት  የመስኖ ልማት የአርሶ አደሩ ዋና የምርት መሰብሰቢያ አማራጭ እየሆነ መጥቷል።

ምርቱ የተሰበሰበውም በመጀመሪያው ዙር ከለማው 91 ሺህ 150 ሄክታር መሬት የደረሰውን ሲሆን ከምርቱም መካከል ቀይ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቀይ ስር፣ ካሮት፣ ድንችና ጥቅል ጎመን ይገኙበታል።

ቀሪው ምርት  ከመሰብሰቡ በተጓዳኝ  በሁለተኛ ዙር 21 ሺህ 800 ሄክታር መልማቱን የቡድኑ መሪ አመልክተዋል፡፡

እንደመጀመሪያው ሁሉ ለሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ከ256 ሺህ በላይ  ስልጠና የወሰዱ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከእነዚሁ ውስጥም 32 ሺህ 900 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

በዞኑ በተያዘው ዓመት እስከ ሶስተኛ ዙር በሚዘልቀው የመስኖ ስራ  ከሚለማው 94 ሺህ 200 ሄክታር መሬትም 14ሚሊዮን 885 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ  ታቅዶ  እየተሰራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በቀወት ወረዳ የአለን ቀበሌ አርሶ አደር ሞገስ ወንድአፈራሁ በሰጡት አስተያየት ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ መስኖ በመጠቀም በየዓመቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት ባለፈው ዓመት በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ካመረቱት 320 ኩንታል ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ካሮት ምርት ሽያጭ ከ350 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት ችለዋል።

በተያዘው ዓመትም በመስኖ ሽንኩርትና ሌላም ሰብል ጨምሮ  ያገኙትን ከ400 ኩንታል የሚበልጥ  ምርት ገበያ አውጥተው በመሸጥ ከ370 ሺህ ብር በላይ መሸጣቸውንም ጠቁመዋል።

በዓመት እስከ ሶስት  ጊዜ በመስኖ እንደሚያመርቱ የተናገሩት አርሶ አደር ሞገስ የውሃ እጥረትና የማዳበሪያ አቅርቦት መጓተት ችግሮች ቢፈቱ ከዚህ በላይ ማምረት እንደሚቻሉም አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ከአንድ ሄክታር መሬት  20 ኩንታል ሰብል አምርተው 30ሺህ ብር በመሸጥ ገቢ ማግኘታቸውን የተናገሩት ደግሞ በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ የአጥቆ ቀበሌ አርሶ አደር የሱፍ ተስፋዬ ናቸው፡፡

በተያዘው ዓመትም እስካሁን ካለሙት  ምርት ሽያጭ 10 ሺህ ብር የሚጠጋ ማግኘታቸውንም አውስተዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ባለፈው ዓመት 86 ሺህ 700 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱም ተመልክቷል፡፡

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን