አርዕስተ ዜና

የደብረታቦር - ጃራገንዶ 88 ኪሎ ሜትር የአስፖልት መንገድ ግንባታ ተጠናቀቀ

150 times

ባህር ዳር ሚያዚያ 8/2010 የደብረታቦር - ጃራገንዶ በአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው 88 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

የመንገዱ መሰራት በእግር ጉዞ ከስድስት ሰዓት በላይ ያደርጉት የነበረውን አድካሚ ጉዞ በተሽከርካሪ ወደ አንድ ሰዓት ዝቅ በማድረግ ከእንግልት እንደታደጋቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

በባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ መንገዱ ትናንት በባለሙያዎች በተጎበኘበት ወቅት እንደገለፁት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ ላይ አጠቃላይ የሃገሪቱ  የመንገድ አውታር 110 ሺህ ኪሎ ሜትር ነበር፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የመንገድ አውታሩን 210 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ ታስቦ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ግቡን ለማሳካትም መንግስት በርካታ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የደረጃ ማሻሻል ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የዚህ መንገድ ግንባታም የእቅዱ አካል መሆኑን አመልክተው፤ ይህም የህዝቡን የዘመናት የመንገድ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አቶ ሳምሶን አስታውቀዋል።

መንገዱ የንኮማንድ በተባለ ሃገር አቀፍ ተቋራጭ እንደተሰራና ሙሉ ወጭው በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ መሆኑንም አብራርተዋል።

የሃገር ውስጥ ተቋራጮች አቅማቸው እያደገ መምጣቱንና በአሁኑ ወቅትም በፌደራል መንገዶች ግንባታ የተሰማሩ 100 የሚሆኑ ተቋራጮች አሉ ብለዋል።

ከዚህ በላይ አቅማቸው እንዲያድግም መንግስት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ምን ሲሰራ ነበር?

የንኮማንድ ኩባንያ ባለቤትና የመንገዱ ተቋራጭ አቶ የምሩ ነጋ በበኩላቸው የአካባቢው መልካምድራዊ አቀማመጥ አስቸጋሪነትና መሬቱ ዋልካ አፈር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግንባታውን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር።

በተለይም ከዲዛይን አለመስተካከል ጋር በተያያዘ ችግር የገጠመ ቢሆንም ችግሩን በመቋቋምና ዲዛይኑን በማስተካከል “መንገዱን ገንብቶ ማጠናቀቅ ተችሏል” ብለዋል።

የመንገዱን ደረጃና ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራ እንደተቋራጭ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ዜጋ በባለቤትነት ለመስራት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በመንገድ ግንባታም ከ5 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን በቀጣይም የመንገዱ ሙሉ ርክክብ እስኪካሄድ በውላቸው መሰረት ችግር ቢኖር ተገቢን ማስተካከያ እንደሚያደርጉ አብራርተዋል።

የመንገዱ ተቆጣጣሪ መሃንዲስ አቶ ሲሳይ ጫላ በበኩላቸው መንገዱ ጥራቱን ጠብቆ እንዲከናወን ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር መደረጉን አመልክተው። 

በዲዛይን መቀየርና በአካባቢው መልካ ምድራዊ አቀማመጥ ችግር ምክንያት የመንገዱ የግንባታ ውል ጊዜ ሦስት ዓመት ቢሆንም ከአንድ ዓመት መዘግየት በኋላ በአራተኛ ዓመቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የመንገዱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ምንአሉ?

በእስቴ ወረዳ ጎሽ በረት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሹመት ምትኩ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ቀደም ሲል የከፋ የመንገድ ችግር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን የመንገዱ መሰራት “ካለመኖር ወደ መኖር የመለሰን ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።

በዚህም ህመምተኞችን ያለምንም ችግር አጓጉዞ በማሳከም ጤንነታቸውን መመለስ እንደተቻለ፣ ዘመድ ከዘመዱ በቀላሉ ሊገናኝ እንደቻለም ተናግረዋል።

መንገዱን ተከትሎም አዳዲስ ከተሞችን መመስረት እንደተቻለ ጠቁመው፤ በዚህም ከገጠር ወደ ከተማ መሸጋገር እንደቻሉና ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በመንገዱ መሰራትም ቀደም ሲል ደብረታቦር ከተማ ለመሄድ በእግር ከስድስት ሰዓት በላይ ይጓዙ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን በመኪና በአንድ ሰዓት መድረስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ላቀው አልታሰብ በበኩላቸው ቀደም ሲል ወደ ከተማ ሲጓዙ በወንዝ ሙላት ይወሰዱ እንደነበርና ገንዘባቸውን በሽፍታ ይቀሙ እንደነበር አመልክተዋል።

አሁን ላይ በመስኖ ያመረቱትን ድንችም ሆነ ሽንኩርት በመኪና በማጓጓዝ በቀላሉ መሸጥ እንደቻሉና የመስኖ ልማታቸውንም ለማስፋፋት እድል እንደፈጠረላቸው ጠቁመው፤ የተሻለ መኪና እንዲመደብላቸውም ጠይቀዋል።

ከደብረታቦር፣ ጅብ አስራ ማርያም ጃራገንዶ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ስራ ትናንት በባለሙያዎች ተጎብኝቷል።

 

 

Last modified on Monday, 16 April 2018 23:51
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን