አርዕስተ ዜና

ባለስልጣኑ በአገሪቱ ያለውን የሃይል ብክነት ለማስቀረት የሚያደርገው ጥረት አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ

156 times

 አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለስልጣን በአገሪቱ ያለውን የሃይል ብክነት ለማስቀረት እየሰራ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤት አለማምጣቱን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባለስልጣኑን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል።

በአገሪቱ ካለው ሃይል በአጠቃቀም ሂደት 26 በመቶ እንደሚባክንና ተቋሙ ይህንን የሃይል ብክነት ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመተባበር ለማዳን እንዲሰራ ተቋቁሟል።

ነገር ግን ተቋሙ የተሰጠውን ዋና ተልዕኮ ለማስፈጸም የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና የተለያዩ የማስፈጸሚያ ጥናቶችን ቢያካሂድም  የሃይል ብክነቱን ለመቀነስ በተሰራው ስራ ተጨባጭ ውጤት አልታየም።

በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ መሆኑን የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር አማረ የሚባክነውን ሃብት ወደ ልማት ቀይሮ የህብረተሰቡን ጥያቄ የመመለስ ስራ ጊዜ የሚሰጠው እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

የኢነርጂ አዋጅ ወጥቶ የማስፈጸሚያ ደንብ ለማዘጋጀት ብቻ አራት አመታትን በማስቆጠሩ ባለስልጣኑ አስገዳጅ እርምጃዎች መውሰድ እንዳይችል ማድረጉ ተጠቁሟል።

በዚህም ምክንያት በተለይ ትልልቅ ሃይል የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች፣ ሆቴሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት የሚያባክኑትን ሃይል

መቆጣጣር አልተቻለም ብለዋል።

መንግስት የተቋሙን አቅም ከኤጀንሲ ወደ ባለስልጣን ቢያሳድገውም እስካሁን አላስፈላጊ ሃይል በሚጠቀሙና ህገ-ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ አልወሰደም ተብሎል ።

ባለስልጣኑ የሃይል ብክነቱን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን አከናውኛለሁ ቢልም ተጨባጭ አድርጎ መረጃውን አለማቅረቡን ገልጸዋል።

በቀጣይ ተቋሙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የቅንጅት ስራ እንዲያጠናከር፣ የኢነርጂ ብቃትና ቁጠባ ደንብን እንዲያፋጠን፣ የተሰጠውን የስልጣን ሃላፊነት በመወጣትና ምክር ቤቱ የሰጠውን ግብረ መልስ መተግበር እንዳለበት አሳስቧል።

ባለስልጣኑ ክልሎችን የማሰልጠን፣  ሪፖርት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ለምክር ቤቱ በመላክና የተጀመሩ የፋይናንስና ኦዲት ግኝቶችን በአፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ተግባርን አጠናክሮ እንዲቀጥልም  ተጠይቋል።

ምክር ቤቱም ከተቋሙ አቅም በላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። 

Last modified on Monday, 16 April 2018 23:37
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን