አርዕስተ ዜና

124ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል ተባለ

149 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ 124ሺ የሚጠጉ ሰዎችን በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረጉን  አስታወቀ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳመነ ጌራወርቅ እንደተናገሩት፤ በመጀመሪያው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ትግበራ ለምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭ የሆኑ 123ሺህ918 ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተለዩ 35 ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝብ ተለይተው በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እንዲሁም በጽዳትና ውበት በመሳሰሉ የማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች እንዲሰማሩ ተደርጎ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛሉ ።

ፕሮግራሙን ከሚታቀፉት ውስጥ 86 በመቶ የሚሆኑት በልማት ስራ ተሳትፎ እያደረጉ የሚጠቀሙ ሲሆን በተለያየ ምክንያት መስራት የማይችሉና የምግብ ዋስትናቸውን ያለረጋገጡ ቀሪዎቹ 14 በመቶዎቹ የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ ናቸው  ብለዋል ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት ካዳመጠ በኋላ በተመረጡ ቀጠናዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ከጎበኙና በምግብ ዋስትና ልማት የማህበረሰብ አቀፍ ልማት ስራዎች ላይ የተሰማሩ ተጠቃሚዎችን ካነጋገሩ በኋላ ኤጀንሲው የተመደበለትን ገንዘብ በአግባቡ ተግባር ላይ ማዋሉን ተመልክተናል ብለዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከመለየት ጀምሮ የተደረገውን ጥረትና የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሌላው የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ እባቡ ብርሌ 'ኤጀንሲው ከሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለምግብ ዋስትና ትግበራ የተመደበለትን ገንዘብ ለታለመለት ተግባር እያዋለው መሆኑን በመስክ ምልከታችን አረጋግጠናል' ብለዋል።

በምግብ ዋስትና ትግበራ ፕሮግራሙ ከተሰማሩት መካከል ወይዘሮ ቀለሟ  ግዛቸውና አቶ ቢሰጥ አለነ ባገኙት እድል ራሳቸውን በመቻላቸው ከምግብ ዋስትና እጦት ችግር መላቀቃቸውን ተናግረዋል።

በማህበረሰብ አቀፍ ልማት ስራው ደስተኛ ቢሆኑም ክፍያው ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል።

በ2ኛው ዙር የምግብ ዋስና ፕሮግራም 200ሺ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ ከታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ በሁሉም ወረዳዎችና ቀጠናዎች በልየታ ኮሚቴዎች አማካኝነት ምዝገባ መካሄዱን ኤጀንሲው አስታውቋል።

በከተሞች እየተካሄደ ያለው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በመላ አገሪቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች እየተተገበረ ይገኛል።

ፕሮግራሙ የሚካሄደው ከዓለም ባንክ በተገኘ 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር እና 150 ሚሊዮን ዶላር መንግስት በመደበው ገንዘብ ሲሆን ዜጎችን ከድህነት ያወጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በአዲስ አበባ በሚካሄደው ፕሮግራም የክፍያ ማነስና የማህበረሰብ ዓቀፍ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል የመስሪያ መሳሪያ አቅርቦት ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበ ነው።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን