አርዕስተ ዜና

በምዕራብ ጎንደር ዞን 391 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን የእርሻ ሥራ ተጀምሯል

170 times

መተማ ሚያዝያ  8/2010 በምዕራብ ጎንደር ዞን በመጪው የመኸር ወቅት 391ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ለመሸፈን ታቅዶ የእርሻ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መመሪያ አስታወቀ።

በግብርና ልማት ሥራው ለውጭ ገበያ ለሚሆኑ ሰብሎች ትኩረት መሰጠቱም ተመልከቷል።

የመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርት ወቅቱ ከሚለማው መሬት ውስጥ እስካሁን 100 ሺህ ሄክታሩ ታርሶ ለዘር ተዘጋጅቷል።

ቀሪውን መሬት ለማረስ የማሳ ጽዳት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

በምርት ወቅቱ ለውጭ ገበያ የሚሆኑ የሰሊጥ፣ የቦለቄና ቅመማቅመም ሰብሎች በስፋት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን የገለፁት ባለሙያው፣ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚሆን ጥጥ እንደሚለማ አመላክተዋል።

ለምርት ማሳደጊያ የሚያገለግል 40 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 1 ሺህ 300 ኩንታል የተለያየ የሰብል ምርጥ ዘር ቀርቦ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ በምርት ወቅቱ ታርሶ በዘር ከሚሸፈነው መሬት 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ።

በዞኑ መተማ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር አስማረ አያና በምርት ወቅቱ 10 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በጥቁር አፈር የእርሻ ማሳቸው ላይ ውሃ እንዳይተኛበትና በሰብል ላይ ጉዳት አንዳይደርስ ውሃ ለማጠንፈፍ የሚረዳቸውን ቦይ ለመክፈት ከወዲሁ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።

" አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ መሬቴን ይጎዳዋል በሚል ማዳበሪያ አልጠቀምም ነበር፤ ከባለሙያ የተሰጠኝን ምክር በመቀበል ዘንድሮ ማዳበሪያ ተጠቅሜ ለመዝራት ተዘጋጅቻለሁ " ያሉት ደግሞ በወረዳው መቃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምህረቱ ፈንቴ ናቸው፡

በወረዳው የደለሎ እርሻ ልማት ባለቤት አቶ ጌትየ ገብሩ በበኩላቸው 200 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥና ጥጥ ለመዝራት የማዳበሪያ ግዥና ሌሎች ቅደመ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል ።

Last modified on Monday, 16 April 2018 21:43
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን