አርዕስተ ዜና

አማራጭ የሽግግር የንብ ቀፎ የማር ምርታችንን አሳድጎልናል--- የሃውዜን ወረዳ አርሶ አደሮች

12 Jan 2018
218 times

መቀሌ ጥር 4/2010 በአነስተኛ ዋጋ እየቀረበላቸው ያለው አማራጭ የሽግግር የንብ ቀፎ ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በትግራይ ክልል ሀውዜን ወረዳ አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ ማር አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።    

የመቀሌ ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የንብ መኖና አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሀውዜን ወረዳ የሰላም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃነ ጸጋይ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ በዋጋ አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ  ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ስለሚቻል በአርሶአደሮች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

ከሸንበቆ የተሰራው አዲሱ የሽግግር ቀፎ ምርታቸውን እንዳሳደገላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በወረዳው የደብረብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጸጋይ መለስ በበኩላቸው፣ በምርምር ማዕከሉ በተሰራው የንብ ቀፎ አጠቃቀም ላይ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከሸንበቆ የተሰራው ቀፎ ለንቦቹ ተስማሚ ሙቀት የሚሰጥ በመሆኑ የማር ምርታቸው እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ንቦቹ ምግባቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአካባቢው ብርድ ምክንያት እንደማይገደብ በ14 የንብ ቀፏቸው ባሉ ንቦች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በመቀሌ እርሻ ምርምር ማዕከል የንብ ተመራማሪ አቶ ሃፍቶም ገብረመድህን እንዳሉት፣ በትግራይ ክልል ለንብ መኖ የሚውሉ የእጽዋት አይነቶችና የሚያብቡበትን ወቅት በጥናት የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እጽዋቱን የማባዛትና ወደ አርሶአደሮች የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ ያለው ነጭ ማር ይበልጥ እየታወቀ እንዲመጣና በብዛት እንዲመረት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ሃፍቶም ገለጻ፣ ከንብ ቀፎ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል በየጊዜው የዋጋ መናር በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

“ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ ተሰርቶ በዝቅተኛ ዋጋ ወደ አርሶአደሩ እየቀረበ ነው” ብለዋል።

ሌላው በማዕከሉ የንብ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ጉዑሽ ጉዲፋይ ፣ በክልሉ “ተበብ፣ ግርቢያና ስዋ ቀርኒ” የተባሉት የእጽዋት አይነቶች ንቦች በዋነኝነት ለምግብነት ከሚጠቀሙባቸው ተክሎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህን እጽዋት በተለያዩ ዘዴዎች በማባዛት  በክልሉ ያለውን የንብ መኖ እጥረት ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ