አርዕስተ ዜና

በማምረቻ ዘርፍ ብንሰማራም ገበያ በማጣት ውጤታማ መሆን አልቻልንም- የማህበሩ አባላት

12 Jan 2018
205 times

ነቀምቴ ጥር 4/2010 በነቀምቴ ከተማ የለጋ ማርጋ ብረታ ብረት መለዋወጫና ማምረቻ አክሲዮን ማህበር አባላት 2 ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ብር  ብድር  ወስደው ወደ ስራ ቢገቡም የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡

የማህበሩ ተወካይ ወጣት አዱኛ ጆቴ  ወደ ስራው ከገቡ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልፆ 72 ዓይነት የተለያዩ ማሽኖች ገዝተው  በማምረት ስራ ቢሰማሩም የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግሯል፡፡

ለገበያው መጥፋት ምክንያት ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት አመቺ ቦታ አለማግኘታቸው ፣ አንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት የራሳቸው የሆነ የብረታ ብረት ወርክሾፕ ማቋቋማቸውና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ቃል የገቡ ተቋማትም ሆነው አለመገኘታቸው ነው፡፡

የማህበሩ አባል ወጣት ተክሉ እሸቱ እንደገለጸው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የማህበሩ አንድ ተስፋ የነበረ ቢሆንም የራሱ የሆነ የብረታብረት መለዋወጫና ማምረቻ ማዕከል በማቋቋሙ ገበያው እንዲጠብ አድርጎታል ።

ከፍንጫአና ከአርጆ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር የተደረገው ስምምነትም እስከ አሁን  የተፈጻሚ  እንዳልሆነ  ወጣት ተክሉ ተናግሯል ።

" መንግስት አደራጅቶና ተገቢውን የማንቀሳቀሻ የብድር አገልግሎት ሰጥቶ ወደ ስራ እንዳስገባን ሁሉ ምርታማነታችንን ጠብቀን ራሳችንን ፣ ቤተሰባችንንና ሀገራችንን እንድንጠቀም ገበያን በማመቻቸት ሒደት ሊያግዘን ይገባል"ብሏል።

የነቀምቴ ከተማ ምክትል ከንቲባ  አቶ አለማየሁ ደሬሳ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በከተማው በተለያዩ የስራ መስኮች ለመሰማራት የተደራጁ ወጣቶች በተደረገላቸው የገበያ ትስስር አብዛኛዎቹ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በለጋ ማርጋ ብረታብረት መለዋወጫ እና ማምረቻ የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር ቢፈጠርላቸውም ስምምነቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ ተጠቃሚዎች አልሆኑም ።

" ችግሩን ለመፍታት   በአካባቢው ከተሞች፣በስኳር ፋብሪካዎችና በአጎራባች ዞኖች ጭምር ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ  እየተሰራ ነው "ብለዋል ።

አቶ አለማየሁ  እንዳመለከቱት በተያዘው  በጀት ዓመት ከ6 ሺህ  ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን  ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የመስሪያ ቦታና ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ