አርዕስተ ዜና

በኢሉአባቦር የቡና ምርትን የሚያሳድጉ 146 ሚሊዮን ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

12 Jan 2018
215 times

መቱ/ፍቼ ጥር 4/2010 በኢሉአባቦር ዞን የቡና ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ የሚችሉ ከ146 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአርሶአደሩና በመንግስት ጣቢያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት በመሳተፍ የመጀመሪያ ምርት ማግኘት መጀመራቸውም ተመልክቷል።

የባለስልጣኑ  ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት የቡና ችግኞቹ እየተዘጋጁ ያሉት በዞኑ 13 ወረዳችዎች ባሉ 9 ሺህ 320 የአርሶአደርና 38  የመንግስት ችግኝ ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡

አዳዲስ ዝርያዎቹ ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ ሲሆን በአግባቡ ከተያዙ በሄክታር ከ12 እስከ 20 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

በቡና ችግኝ ዝግጅቱ ከ26 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንድ ሺህ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

እየተዘጋጁ ያሉት የቡና ችግኞች በመጪው ክረምት በ21 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የሚተከሉ ናቸው።

የግብርና ባለሙያዎች ዘሩን ከመዝራት ጀምሮ በችግኝ አያያዝና እንክብካቤ ላይ ለአርሶአደሩ በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም አቶ ከተማ አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ  በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት በመሳተፍ የመጀመሪያ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን አአስታውቋል።

የባለስልጣኑ የሰሜን ሸዋ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጅማ እንዳሉት በዞኑ ሰባት ወረዳዎች በሚገኙ 113 ቀበሌዎች የሚኖሩት አርሶ አደሮች ምርቱን ያገኙት ባለፉት ሦስት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ካለሙት የቡና ችግኝ ነው።

በየዓመቱ የሚቀርብላቸውን ሁለት መቶ ሺህ የቡና ችግኞች በመጠቀም የቡና ልማቱን በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ዘንድሮም  በዞኑ ችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ 700 ሺህ የቡና ችግኞች ለአርሶ አደሮች እንደሚሰራጩ አመልክተዋል ።

በሰሜን ሸዋ ዞን የቡና እርሻን በስፋት ለማካሄድ በባለሙያዎች ጥናትና ምርምር እየተካሔደ ሲሆን እስካሁንም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ተመርቶ ለቤት ውስጥና ለአካባቢ ፍጆታ መዋሉ ተመልክቷል ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ