አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ጎጃም በ572 ሺህ 200 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ ሰብል ተሰበሰበ

12 Jan 2018
191 times

ደብረ ማርቆስ ጥር 4/2010 በምስራቅ ጎጃም ዞን በመኽር እርሻ በ572 ሺህ 200 ሄክታር ማሳ ላይ የለማ ሰብል በወቅቱ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ እያለ ዳኘ ለኢዜአ እንደተናገሩት በ2009/2010 የመኽር ወቅት በ640 ሺህ ሄክታር መሬት  ከለማው ሰብል 90 በመቶ የሚሆነው በወቅቱ ተሰብስቧል።

ሰብሉን በምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነርና የአርሶ አደሮችን የልማትና የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመጠቀም ለመሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።

አቶ እያለ እንዳሉት ከተሰበሰቡ የሰብል ምርቶች መካከል ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ገብስ፣ አተር፣ ባቄላ፣ ቦለቄና ሰሊጥ ይገኙበታል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት የተገኘ ሲሆን ምርቱ ቀድሞ በተሰበሰበባቸውና ውሃገብ በሆኑ ማሳዎች ላይም የበጋ መስኖ ልማት ሥራው እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ እያለ እንዳሉት፣ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብና በተደራጀ አግባብ መንቀሳቀሱ የምርት ብክነትን ለመቀነስ አስችሏል።

በዞኑ አዋበል ወረዳ የሸብላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታረቀኝ መለሰ እንዳሉት፣ ሰብላቸውን በወቅቱ በመሰብሰባቸው ምርታቸውን ከዝናብና ከውርጭ መታደግ ችለዋል።

"በመኽር ወቅት የዘራሁትን ሰብል ሰብስቤ በመጨረስ በበጋ የመስኖ ልማት ገብስና ድንች በማሳዬ ላይ ዘርቺያለሁ" ያሉት ደግሞ  በጎዛምን ወረዳ የቀቢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አይርሳው ጓሌ ናቸው።

"ባለፈው ዓመት በመኽር ያለማሁትን ሰብል ዘግይቼ በመሰብሰቤ በመስኖ ያለማሁት ድንች የውሃ እጥረት አጋጥሞት ነበር አሁን ግን የውሃው መጠን ሳይቀንስ ቀድሜ መዝራት ስለቻልኩ ተጠቃሚ መሆን እችላለሁ" ሲሉም አርሶ አደሩ ተናግረዋል።

በዞኑ በመኽር ወቅት ከለማው ማሳ ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ