አርዕስተ ዜና

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከ16 ሺ በላይ ቤቶችን ሊገነባ ነው Featured

12 Jan 2018
187 times

አዲስ አበባ ጥር 4/2010 የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከ16 ሺ በላይ ቤቶችን ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ ለቤቶቹ የግንባታ ስራ የዲዛይን ክለሳ፣ የአዳዲስ ዲዛይኖችና የአፈር ምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ከተመረጡ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።

ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱን የተፈራረመው ኖሚ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የወሰነ የግል ማህበርና ጂ አይ አማካሪ ድርጅት ጋር ነው።

ድርጅቶቹ ለግንባታው የሚረዳ የዲዛይንና የአፈር ምርመራ ስራዎችን በተመረጡ ተቋማት ይዞታ ስር ባሉና ከከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ አዳዲስ ቦታዎች ይከናውናሉ።

በኮርፖሬሽኑ የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ግሩም ብርሃኑ እንደገለጹት የዲዛይንና የአፈር ምርምር ስራው በሁሉት ወራት ውስጥ ተጠናቆ በተያዘው ዓመት መጨረሻ የቤቶቹ ግንባታ ይጀመራል።

የሚገነቡት ቤቶች ለመንግስት ሰራተኞች፣ ለመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በኪራይ መልክ የሚተላለፉ ሲሆን፤ ከመኖሪያነት በተጨማሪ ለንግድ የሚሆኑ ክፍሎችንም እንደሚያካትቱ ጠቁመዋል።

በአጠቃለይ ከ16 ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገነቡ የተናገሩት አቶ ግሩም፤ "ለግንባታ ስራው  ማከናወኛ 30 ቢሊዮን ብር ተመድቧል" ብለዋል።

ቤቶቹ ከ35 ሜትር በላይ ከፍታና 9 ወለል ህንጻዎች ሲሆኑ፤ ከ1 እስከ 4 መኝታ ክፍሎች ይኖራቸዋል።

የቤቶቹን ግንባታ በ3 ዓመት ጊዜ ወስጥ በማጠናቀቅ በተመጣጣኝ ዋጋ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደም አክለዋል።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በከተማዋ እየጨመረ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ከማቃለል አንጻር በቤት ልማትና አቅርቦት ላይ መሳተፍ በሚያስችለው መልኩ በሚንስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 389/2009 የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ