አርዕስተ ዜና

ሃገራችን ለሃር ልማት ምቹ ስነ-ምህዳር ቢኖራትም የሚፈለገውን ያክል ምርታማ አይደለችም...የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር Featured

03 Jan 2018
411 times

አዳማ ታህሳስ 25/2010 የሃገራችን የግብርና ስነ-ምህዳር ለሃር ልማት ምቹ ቢሆንም ከዘርፉ የሚገኘው ምርት የሚፈለገውን ያክል እንዳላደገ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ።

የሀር ልማትን ይበልጥ ለማዘመንና ለማሳደግ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢፌዴሪ እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገብረኢግዝአብሔር ገብረዮሓንስ ለኢዜአ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ እየተከናወነ ያለው የሐር ልማት እጅግ አነስተኛ ነው ።

ልማቱ በግለሰቦች በገቡት የጉሎና የእንጆሪ ሐር ትል ዘሮች አማካይነት የሚካሔድ መሆኑን ገልፀው በዘርፉ በተደረገው ጥናት ከነዚህ የሚገኘው ኩብኩባና የሐር ድር  ምርት መጠን በጣም አነስተኛና ጥራቱም ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ከውጭ ሀገር የሚገቡ የሐር ትሎች ዲቃላ በመሆናቸው ከአንድ ትውልድ በኋላ የሐር ምርታቸውና የኩብኩባ መጠናቸው እየቀነሰ እንደሚሔድ ገልጸው ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ራሱን የቻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

መንግስት የዘርፉን ልማት ለማስፋፋትና ለማሳደግ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል አሰራር፣አደረጃጀትና የህግ ማዕቀፎችን እየዘረጋ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከውጭ ሀገር በሚገቡ ድቅል የሐር ትል ዘሮች የዘርፉን ልማት በተገቢው መንገድ ለማከናወን አዋጭ ባለመሆኑ የሀገር ውስጥ የሐር ትል ወላጅ ዘር ጣቢያ ተቋቁሞ በማራባትና በማባዛት ለተጠቃሚዎች የሚሰራጩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

"በዋናነት ለግብርና ስነ-ምህዳራችን ተስማሚ የሆኑ ድቅል የሐር ትል ዘሮችን የመለየት፣ምርታማ የሆኑትን በመምረጥ በመንግስትና በባለሃብቶች ማዳቀያ ጣቢያዎች እንዲራቡና እንዲባዙ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይገባል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ በበኩላቸው "ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የሐር ልማት ለማከናወን መልካሳ ግብርና ምርምር ማእከል ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው"  ብለዋል።

በማዕከሉ የሐር ትል ዝርያዎችን መሰረት በማድረግ የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የጉሎና የእንጆሪ መኖ ልማት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

"ለሐር ትል ልማት የሀገራችን የግብርና ስነ ምህዳር ተስማሚ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ ድቅል የሐር ትሎችን ከውጭ ሀገር በማስገባት የማላመድ፣ምርታማ የሆኑትን በምርምር የመለየትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ