አርዕስተ ዜና

በዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ የወርቅ ፋብሪካ ማምረት ጀመረ Featured

03 Jan 2018
434 times

መቐለ ታህሳስ 25/2010 በዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘውና በኢዛና የማዕድን ኩባንያ የተገነባው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ።

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ አስገደ ፅምብላ ወረዳ ልዩ ስሙ ሚሊ በተባለ ቦታ የተገነባው የወርቅ ፋብሪካ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋይ አሰፋ ገልጸዋል።

ፋብሪካው በ20 ሄክታር መሬት ላይ የተተከለና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያሟላ ሲሆን በቀን 840ቶን አፈር በመፍጨት ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ወርቅ እንደሚያመርት ገልጸዋል።

በዓመት 1ሺህ 300 ኪሎ ግራም በማምረት ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሃገሪቱ እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን ሶስት ኪሎ ግራም በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

"ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ተጨማሪ ባለሙያዎችን ከውጭ በመቅጠርና ልምድ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ ማምረት ሲጀምር በቀን ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ያመርታል"ብለዋል።

ፋብሪካው የአካባቢ ብክለት እንዳያስከትል በ10 ሚሊዮን ብር የፍሳሽ ማስወገጃ እንደተዘጋጀለትም ተናግረዋል።

የፋብሪካው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን አወጣሀኝ " ፋብሪካው የተተከለበት ቦታ ከአምስት ዓመት በላይ በውጭና የሃገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች አዋጭነቱ ተረጋግጧል" ብለዋል።

በአካባቢው በተደረገው የአፈር ምርመራ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሜትር ጥልቀት የወርቅ ክምችት እንደሚገኝ በጂኦሎጂ ጥናትና የላብራቶሪ ምርመራ መረጋገጡንም አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ200 ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሲጀምር የመቀበል አቅሙን ከ300 በላይ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በባህላዊ የወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩትን በማደራጀትም የሰበሰቡትን ወርቅ ባለው ገበያ ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን ጨምሮ ቀለል ያሉ የወርቅ መፈተሻ መሳሪያዎችንና የኬሚካል ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የኢዛና ማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ አታኽልቲ አርአያ በበኩላቸው ወርቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የማዕድን ቁፋሮዎችን ለማካሄድ ከውጭ ሃገር የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በመሆን እያጠና እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሚሊ የተተከለው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ በሃገራችን ከ33 ዓመት በፊት ከተተከለው የአዶላ የወርቅ ፋብሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ