አርዕስተ ዜና

በማእከላዊ ጎንደር ዞን በ434ሺ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብል በውርጭ ሳይጎዳ ተሰበሰበ

03 Jan 2018
396 times

ጎንደር ታህሳስ 25/2010 በማእከላዊ ጎንደር ዞን የደረሱ ሰብሎችን ከዝናብና ከውርጭ ጉዳት ለመታደግ አርሶ አደሩ ባደረገው ጥረት በ434ሺ ሄክታር መሬት የደረሱ ሰብሎች መሰብሰባቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ በ2009/10 ምርት ዘመን ከለማው በ484ሺ ሄክታር 89 ነጥብ ስድስት በመቶ የሚሆነውን መሰብሰብ ተችሏል።

ከተሰበሰቡ የደረሱ ሰብሎች መካከል ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ የቢራ ገብስና የቅባት ሰብሎች እንደሚገኙበት የገለጹት ኃላፊው የአርሶ አደሮቹ የልማት ቡድኖች ስራውን በተቀናጀ መልኩ ለማቀላጠፍ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

"በጠገዴና በታች አርማጭሆ ወረዳዎች በምርት ዘመኑ በሰሊጥ ከተሸፈነው ከ100ሺ ሄክታር በላይ መሬት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጠው የሰሊጥ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ የተዘራውን ሰብል አርሶ አደሩ ያዳበረውን በጋራ የማረስ፣የመዝራትና የማረም ልምድ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ እንዳገዘ ተናግረዋል።

በምርት አሰባሰብና አቀማመጥ ወቅት የሚስተዋለውን የድህረ ምርት ብክነት ለመቀነስም ለአርሶ አደሩ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በልማት ጣቢያ ባለሙያዎች አማካኝነት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለይ በአውድማ፣ በንፋስና በእንስሳት እንዲሁም በጎተራ በማስቀመጥ በአይጦችና በተባይ የሚደርሰውን የምርት ብክነትና ጉዳት ለመከላከል የሚረዳ ትምህርት ተሰጥቷል።

በጭልጋ ወረዳ የጮንጮቅ ቀበሌው አርሶ አደር ደሴ አስማረ "በአካባቢው ማለዳ ላይ የሚስተዋለው ውርጭ በደረሱ ሰብሎች ላይ የምርት ጥራት መጓደል የሚያስከትል በመሆኑ አዝመራዬን ሰብስቤ ወደ ጎተራ ማስገባት ጀምሬአለሁ" ብለዋል።

"በህዳርና በታህሳስ ወር የሚከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ውርጭ ቀድሞም ምርት የሚያበላሽ በመሆኑ ጥንቃቄ አደርጋለሁ" ያሉት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የዳስ ድንዛዝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይደግ መላኩ ናቸው።

"የደረሱ ሰብሎችን በደቦና ቤተሰብን ጭምር በማሳተፍ በአግባቡ አጭዶ በመከመርና በመውቃት የምርት ብክነትና ጥራት መጓደል ሳይደርስ ሰብሌን መሰብሰብ ችያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

በዞኑ በምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 484ሺህ ሄክታር መሬት ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ