አርዕስተ ዜና

በሰሜን ሸዋ ዞን 14 ሺህ 800 ሴቶችና ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደረገ

03 Jan 2018
391 times

ፍቼ ታህሳስ 25/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት አራት ወራት በማህበር የተደራጁ 14 ሺህ 8ዐዐ  ሴቶችና  ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደረገ፡፡

የዞኑ የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ተፈሪ ቦጋለ እንደገለጹት ስራ አጥ የነበሩት ወጣቶችና ሴቶች ተደራጅተው  ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገው ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ፣ የስልጠናና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ተመቻችቶላቸው ነው፡፡

እነዚህ ሴቶችና ወጣቶች የመንቀሳቀሻ ገንዘብ በማጣት ሲቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው በ123 ማህበራት ተደራጅተው በመንግስትና በሕዝብ በተደረገላቸው ድጋፍ በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተሰማሩባቸው የስራ መስኮችም የከተማ ግብርና ፣ ማዕድን ማውጣት አነስተኛ ኢንዱስትሪ፣ ግንባታ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድና አገልግሎት ዘርፎች ናቸው ።

የስራ እቅዳቸውን መነሻ በማድረግ እስከ 650 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር እንደተሰጣቸው ያመለከቱት ኃላፊው  ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብቻ 10  ሚሊዮን ብር መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

በማህበር የተደራጁት ሴቶችና ወጣቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤትና እርካታ እንዲያገኙ በማሰብ ከ12 ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል ።

በወረጃርሶ ወረዳ የኑኑ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ጌታቸው ሰማ ከጥቂት ወራት በፊት ሥራ አጥ እንደነበር ጠቅሶ መንግስት የወጣቶችን ችግር በመገንዘብ ያመቻቸው የብድር ገንዘብና ሥልጠና ከሥራ አጥነት አላቆ የራሱን ገቢ እንዲያገኝ እድል እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በስሙ  በተሰየመው የጠጠርና አሸዋ ማምረት ሥራ ከሌሎች 11 ጓደኞቹ ጋር ተሰማርቶ በወር እስከ 2 ሺህ 5ዐዐ ብር ገቢ እንደሚያገኝና የካፒታል አቅሙን  እያሳደገ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም የአካባቢያቸውን ሁኔታ በማጥናት ያገኙትን ስራ ቢሰሩ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውን ችግር በመፍታት ጭምር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁሟል ።

በግሉ ማመልከቻ ባስገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተደራጅቶ የብድርና የስልጠና ድጋፍ ከማግኘት በተጨማሪ ፍቃድ አውጥቶ ከሶስት ወራት በፊት በብረታ ብረት ሥራ መሰማራቱን የተናገረው ደግሞ በፍቼ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሶስት ነዋሪው ወጣት ስለሺ ጐንፋ ነው፡፡

በግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ ነዋሪዋ ወጣት ትግስት አለኸኝ በበኩሏ በቅርቡ  ከአምስት አጋሮቿ ጋር በማኑፋክቸሪንግ ሥራ መሰማራቷን ገልጻለች፡፡

መንግስት የሴቶችን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል የጀመረው ጥረት መንግስታዊ  ባልሆኑ አካላት ጭምር  ሊታገዝ እንደሚገባም ጠቁማለች፡፡

"በተለይ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያሉትን  ችግሮች ለመፍታት  ከድርጅቶችና ከሕብረተሰቡ ብዙ ይጠበቃል "ብላለች ።

ባለፉት አራት ወራት በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡት ወጣቶች መካከል 5 ሺህ 100   የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ የዞኑ የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ