አርዕስተ ዜና

አቢሲኒያ ኤክስፖርት ቄራ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የከብት አድላቢ ማህበራት 8 ሺህ ከብቶችን ሊረከብ ነው Featured

03 Jan 2018
327 times

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 አቢሲኒያ ኤክስፖርት ቄራ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን  ከሚገኙ 20 የከብት አድላቢ ማህበራት ከብቶችን ለመረከብ ስምምነት ፈጸመ።

አቢሲኒያ ኤክስፖርት ቄራ ድርጅት የደለቡ የዳልጋ ከብቶችን በመረከብ ስጋ ወደ ተለያዩ አገራት የሚልክ አገር በቀል ተቋም ነው።

በዚህም ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን  ከሚገኙ 20 የከብት አድላቢ ማህበራት ጋር ለስምንት ወራት የሚቆይ የከብት ግዥ ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሰረትም ማህበራቱ በወር 1 ሺህ የደለቡ ከብቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ድርጅቱ የማጓጓዙን ስራ በራሱ ወጪ የሚያከናውን ይሆናል።

የአቢሲኒያ ኤክስፖርት ቄራ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው ስምምነቱ ምርቱን በቋሚነት ወደ ውጪ ለመላክ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።

ቄራው የደለቡ ከብቶችን ካልተቀበለ ለማድለቢያ የሚወጣውን ወጪ እንደሚሸፍንና የደለቡ ከብቶች ለእርድ ደርሰዋል ብሎ ካመነ ከ 2 ወራት በታችም መውሰድ እንደሚችል ተጠቅሷል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን እንዳሉት ስምምነቱ የስጋ ምርትን ወደ ውጪ አገራት በመላክ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ የሚያሳድግ ነው።

የተደረገው ስምምነት የሚበረታታ ሲሆን ሌሎች ማህበራትም ተመሳሳይ ተግባር በመፈጸም ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ሁሉቱም ወገኖች ስምምነቱን በማክበር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙ ወጣቶች ከዚህ በፊት ከብቶችን ካደለቡ በኋላ  የገበያ ችግር እንደነበረባቸው ገልጸው አሁን ችግሩን የሚቀርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

ስምምነቱን ከተፈራረሙት ማህበራት መካከል ከጊንቢቹ ወረዳ የመጣው የኢፋ ጊምቢቹ የከብት አድላቢዎች ማህበር ኃላፊ ወጣት ዴሲሳ ገለቶ ከዚህ በፊት ከብቶች ቢያደልቡም የገበያ ችግር በመኖሩ ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር ገልጿል።

የገበያ ትስስሩ ቢፈጠርም የመኖ ዋጋ ውድነት፣የሚደልቡ ከብቶችን ከቦረና ዞን ሄደው ሲገዙ ህገወጥ ደላሎች ገበያውን ስለሚያስወድዱባቸው መንግስት ይህንን ችግር እንዲፈታላቸውም ወጣቶቹ ጠይቀዋል።

በስምምነቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ገመቺስ መላኩ በበኩላቸው መንግስት የማህበራትን የገበያ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

መንግስት ወጣቶቹ የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ አገራት የሚላከው የስጋ ምርት በ2000 ዓ.ም ከነበረበት ከ4800 ቶን በ2009 ዓ.ም ወደ 20 ሺህ ቶን ማደጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ