አርዕስተ ዜና

እየተገነቡ ለሚገኙ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥሬ ምርቶችን የሚያመቻች ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጀ

07 Dec 2017
737 times

ሽሬ እንዳስላሴ ህዳር 28/2010 በአራት ክልሎች በመገንባት ላይ ለሚገኙ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በግብአትነት የሚጠቀሙባቸው ጥሬ ምርቶችን ለማመቻቸት የሚያስችል ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን የእንስሳትና ዓሳ ኃብት ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

 በስትራተጂክ እቅዱ ዙሪያ በሸሬ እንዳስላሴ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

 ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ገብረእግዛቢሔር ገብረዮውሃንስ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት በትግራይ ክልል የባእከር ኢንዱስትሪ ፓርክን  ጨምሮ በኦሮምያ ክልል  ቡልቡላ ፣ በአማራ ክልል በቡሬ ፣ በደቡብ ደግሞ  በይርጋለም  ከተማ  የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስቱሪ ፓርኮች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

 ግንባታቸው ከ5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተካሄዱ ያሉት እነዚሁ ፓርኮቹ   ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የማምረት ሥራ ይጀምራሉ ተብለው ይጠበቃል፡፡

 የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቆ ወደ ማምረት ሲሸጋገሩ  የሚፈልጉት የግብርና ምርት በመጠን፣ በፍጥነትና በጥራት ዓመቱን ሙሉ ሳይቆራረጥ ማቅረብ የሚያስችል የሦስት ዓመት ስትራተጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

 ከእቅድ ዝግጅቱ ጋር  ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የግብርና ባለሙያዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊ የሆኑበት የምክክር መድረክ  በየደረጃው በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የተካሄደው የውይይት መድረክም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ፓርኮቹ  የማምረት ስራ ሲጀምሩ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ  በማቅረብ ተጠቃሚ  እንደሚሆን የገለፁት ደግሞ  በኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቱት ዳይሬክተር አቶ ከሊፋ ሁሴን ናቸው።

 አግሮ እንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚፈልጉትን እንስስትና የእንስስት ውጤቶች ዓመቱን ሙሉ ሳይቆራረጥ እንዲያገኙ ለአርሶ አደሮች ከወዲሁ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 በትግራይ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጀማል ግደይ በበኩላቸው በክልሉ በባእከር እየተገነባ ያለው የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚያስፈልገውን ግብአት በአስተማማኝ መልክ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በአግሮ እንዱስትሪ ፓርኩ አቅራቢያ የሚገኙ  የሦስት ዞኖች አርሶ አደሮችና  የህብርት ሥራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችላቸው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በሽሬ እንዳስላሴ ለአምስት ቀናት  በተካሄደው የምክክር መድረክ  የግብርና ባለሙያዎችና የህብረት ሥራ ማህበራት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል። 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ