አርዕስተ ዜና

ጣሊያን ለኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ድጋፍ የሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

07 Dec 2017
430 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 ጣሊያን ለኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ድጋፍ የሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች።

የጣሊያን ልማትና ትብብር ኤጀንሲ በኦሮሚያ ክልል የግብርና ስራዎችን መደገፊያ የ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት የክልሉ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጋለች።

በክልሉ የግብርና ምርት እድገትና ጥራት ማምጣትን አላማ ያደረገው ይህ ፕሮጀክት በአርሲ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች እና በሌሎች ሀያ ተጨማሪ ወረዳዎች ፕሮጀክቱ እንደሚተገበር ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ የዱረም ስንዴ እና የቲማቲም ምርት ማቀነባበሪያ የምርት እድገትና ጥራት በማሳደግ ኢንዱስትሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ግብዓት እንዲያገኙ ከማገዝ በተጨማሪ በአምራቾችና በፋብሪካዎች መካከልም ትስስር ይፈጥራል።

በአምራች ማህበራት የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እና የምግብ ዓይነቶችን በማብዛት የአመጋገብ ስርዓትን ማዘመን የፕሮጀክቱ አካል መሆኑም ተገልጽዋል፡፡

የኦሮሚያ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶሎሳ ገደፋ በዚህ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ ያለውን የስንዴ ምርት ጥራት በማሳደግ ኢንዱስትሪዎች በበቂ ሁኔታ ግብዓት እንዲያገኙ እገዛ ያደርጋል፡፡

በተለይ ሴቶችና ወጣቶች በምርት ሂደት ላይ ተሳታፊነታቸውን በማሳደግ ጠንካራ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ፕሮጀክቱ ያግዛል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በሚያካትታቸው አካባቢዎች እየተገነባ ያለው መቂ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በቀጣይ የስንዴና የቲማቲም የምርት ውጤቶች እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የጣሊያን ልማትና ትብብር ኤጀንሲ ኃላፊ ጂኔቭራ ሌቲዚያ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ በተመረጡ አካባቢዎች የሚያደርገው የስልጠና እና የፋይናንስ ድጋፍ የግብርናውን ዘርፍ እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ምርምር ተቋማትን በፋይናንስ በመደገፍ ምርጥ ዘሮችን በጥናትና ምርምር እንዲደገፉ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ የፕሮጀክቱ አካል መሆኑን ሃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

በተለይም አርሶ አደሮች የዱረም ስንዴን ጥራት እንዲያሻሽሉ በማገዝ የፓስታ ምርትን ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ ከማቅረብ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለማድረግም ድጋፍ እንደሚደረግ ጂኔቨራ ሌቲዚያ ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ 16 ሺህ አባላት ያላቸው 42 የህብረት ስራ ማህበራትን እንዲሁም የዘርፉን ተዋናዮች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ