አርዕስተ ዜና

በአማራ ክልል ቅርሶችን ለመጪው ትውልድ በአግባቡ ለማስተላላፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቆመ Featured

07 Dec 2017
425 times

ባህር ዳር ህዳር 28/2010 በአማራ ክልል ለዘመናት ተጠብቀው የቆዩና የማይተኩ ቅርሶችን ለመጪው ትውልድ በአግባቡ ለማስተላለፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

 የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ ቅርሶችን ለመጠገንና ለመንከባከብ የዘርፉ ባለሙያና የበጀት እጥረት ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ተግልጿል።

 የቋሚ ኮሚቴው የቡድን መሪ አቶ ግርማ መላኩ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት ታሪካዊ ቅርሶች በአያያዝና እንክብካቤ ጉድለት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው።

 መንግስት ቅርሶችን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከቅርሶች ብዛትና ዓይነት አንጻር በሚፈለገው መጠን እየተሰራ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

 የላል ይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ቅርሶች በተለያየ ምክንያት ለጉዳት የተጋለጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ቀደም ሲል ለመጠገን የተደረገው ጥረትም ችግሩን እንዳባባሰው ተናግረዋል።

 በመሆኑም ቅርሶች በተሰሩበት ቁስ በጥንቃቄ መልሶ በመጠገንና በመንከባከብ ለመጪው ትውልድ በአግባቡ የማስተላለፍ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

 የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ልኡል ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ነባርና ጥንታዊ ቅርሶችን መልሶ ለመጠገን የቴክኖሎጂ እጥረት ችግር እንዳለ ገልጸዋል።

 ከእዚህ በተጨማሪ በሙያው ሃገራዊ እውቀት ያለው ባለሙያና የበጀት እጥረት ቅርሶችን በአግባቡ ለመጠገን እንቅፋት መሆኑን አስታውቀዋል።

 ቅርሶችን በመጠበቅና በመንከባከብ በሚደረገው ጥረትም ሕብረተሰቡ ከመንግስት ባልተናነሰ በገንዘቡ፣ በጉልበቱና በእውቀቱ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ልዑል አሳስበዋል።

 ቋሚ ኮሚቴው ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር ባደረገው የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ከአማራ ክልል የተለያዩ ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ