አርዕስተ ዜና

የተሻሻሉት የሰብል ዝርያዎች የአርሶ አደሮችን ምርታማነት አሳድገዋል

18 Nov 2017
751 times

አዲስ አበባ ህዳር 9/2010 የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በመጠቀማቸው ምርታማነታቸው መጨመሩን በኦሮሚያ ክልል የባኮ አካባቢ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በክልሉ በሚገኙ ሁለት የምርምር ማዕከላት ወጥተው በብሔራዊ ዘር አጽዳቂ ኮሚቴ የተገመገሙ 13 አዳዲስ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸው ተገልጿል።

ከዝርያዎቹ መካከል የፓስታ፣ የመኮሮኒና የአጃ ስንዴ፣ የዳጉሳ፣ የባቄላ፣ የአተር፣ የሰሊጥ፣ የሩዝ፣ የቲማቲምና የእንስሳት መኖ ይጠቀሳሉ።

ከአንድ ሺህ በላይ አርሶና አርብቶ አደሮችም ዝርያዎቹን በማልማት ላይ ይገኛሉ።

አርሶ አደሮቹ የተሻሻሉት ዝርያዎች በትንሽ መሬት ብዙ ምርት እንዲያገኙ እንዳስቻሏቸው ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

አርሶ አደር አይሻ መሃመድ እንዳሉት ምርጥ ዘሩን ካገኙ ጀምሮ በትንሽ ቦታ የሚያመርቱትን ምርት ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

አርሶ አደር ሻፊ አለሙም በባለሙያ እገዛ የዳጉሳ ሰብላቸውን በመስመር በመዝራታቸው የተሻለ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የኮምዩኒኬሽንና የፓርትነርሺፕ የሥራ ሂደት ሥራ አስኪያጅ አቶ የወንድወሰን ቢቂላ በበኩላቸው ለአርሶ አደሮች የተሰራጩት አዳዲስ ዝርያዎች ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጋቸው በላይ ለአካባቢ ስነ-ምህዳር ተስማሚ እንደሆኑ ገልጸዋል።

አዲስ የተሻሻለው የዳጉሳ ዝርያ ቀደም ሲል በሄክታር ከሚሰጠው ምርት የ18 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ለአብነት አንስተዋል።

የምርምር ሥራቸው ተጠናቆ ለአርሶ አደሩ ከተሰራጩት የሰብል ዝርያዎች መካከል የሩዝና የዳጉሳ ሰብሎች ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝተው በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

'ጨዋቃ' የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የሩዝ ዝርያ በደረቅ መሬት በዝናብ ወይም በመስኖ ሊለማ የሚችል ነው።

ይህን የሩዝ ዝርያ በስፋት በማልማት ላይ የሚገኙት የኢሉአባቦራ ዞን ጨዋቃ ወረዳ አርሶ አደሮች የምግብ ፍላጎታቸውን ከመሸፈን ባሻገር ለሌሎች ክልሎች ዘር እስከ ማቅረብ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

"የምርምር ተቋሙ ለአርሶ አደሮቹ ከቅድመ እስከ ድህረ ምርት ባለውን ሂደት ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል አቶ የወንድወሰን።

ሩዙ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

በዘር ብዜት ሥራ የተሰማሩ መንግሥታዊም ሆነ የግል ተቋማት እነዚህን ሰብሎች ለተጠቃሚ በማድረሱ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል።

በኢንስቲትዩቱ የግብርና እድገት ፕሮግራም የምርምር ዘርፍ የክልሉ አስተባባሪ ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ በበኩላቸው እንደገለጹት የፕሮግራሙ ዓላማ አርሶ አደሮች በምርምር የተገኙና ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሰብሎችን በማልማት ኑሯቸውን እንዲያያሻሽሉ ማድረግ ነው።

"አርሶ አደሮችም ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት መስራት አለባቸው" ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ የዕፅዋትና የእንስሳት፣ የማዳበሪያና የአፈር ለምነት አጠቃቀም፣ የአስተራረስ ዘዴና የመሳሰሉት ላይ በዓመት እስከ 60 የሚደርሱ የቴክኖሎጂ ዝርያዎችን እንደሚያወጣ ተመልክቷል።

ኢንስቲትዩቱ ሶስት የግብርና ምህንድስና፣ አራት የአፈር ምርምር፣ አንድ የንብና አንድ የዓሣ ምርምር ቀሪዎቹ የእንስሳት፣ የተፈጥሮ ሃብትና የሰብል በድምሩ 17 የግብርና ምርምር ማዕከላትን በስሩ ይዟል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ