አርዕስተ ዜና

የአየር ንብረት ለውጥን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሜትሮሎጂ ትንበያ መረጃ ለአርሶ አደሩ ለማደረስ ጥረት እየተደረገ ነው

14 Nov 2017
789 times

አዳማ ህዳር 5/2010 የአየር ንብረት ለውጥ በግብርናው ስራ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሜትሮሎጂ  ትንበያ መረጃ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴሽን ልማት ዳይሬክተር አቶ ወንድያለህ ሀብታሙ እንደገለፁት የሜትሮሎጂ  ትንበያና ምክረ ሃሳብ ወቅቱን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ 

ይህም የመረጃ ፍሰቱን በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት፣ፈጣን፣ወቅታዊና ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያ ለአርሶ አደሩ  ተደራሽ በማድረግ ላይ የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ  ያስችላል፡፡ 

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ  ሀገሪቱ  የደረሰችበትን  የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት መሰረት ያደረገ የሜትሮሎጂ  ትንበያ፣ የመረጃ ፍሰት ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ ለአርሶ አደሩ ለማዳረስ የተቀናጀ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም ሚኒስቴሩ ፣የግብርና ትራንስፎርሜሽንና የሜትሮሎጂ  ኤጄንሲዎች የጋራ ግብረ ሃይል አቋቁመው እየሰሩ ናቸው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የአየር  እርጥበት፣በኤልኒኖና ላኒኖ ክስተት ላይ የተሟላ መረጃ በመስጠት ሀገሪቱ በድርቅና ጎርፍ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መቀልበስ እንዲቻል የሜትሮሎጂ ትንበያ መረጃ  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው።

የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጄንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ በበኩላቸው  ኤጄንሲው በሀገሪቱ  1ሺህ 300 በሰው የሚመዘገቡ የአየር ትንበያ መሳሪያዎችና በ240 አውቶማቲክ መመዝገቢያ ማዕከላት መረጃ በመሰብሰብ ለህብረሰተቡ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጤና፣ትራንስፖርት፣ግብርና፣የአየር ንብረት ተለዋወጭነት ባህሪያት ተፅእኖና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የሜትሮሎጂ ምክረሃሳቦችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ኢሳያስ ለማ እንደገለፁት በአየር ትንበያ፣በሰብል በሽታዎች መከላከል፣በዓመቱ ሊኖር የሚችለው የዝናብ መጠን፣የቅድመ ምርትና ድህረ ምርት ትንበያዎች ሲያከናወን ቆይቷል፡፡ 

በዚህም በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብና ትግራይ ክልሎች ለአርሶ አደሩ ምርት ውጤታማነት አስተዋፅኦ እንደነበረው አመልክተዋል።

በየ10 ቀናት የአየር ፀባይ ትንተና በማድረግና ምክረ ሃሳቦችን አደራጅቶ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት በተፈጥሮ ሀብት፣በእርጥበት አያያዝ፣በውሃ ማቋር፣በአፈር ጥበቃና በደን ልማት ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ማድረግ ተችሏል አስችሏል።

በዞንና በወረዳ ደረጃ የአየር ፀባይ ትንበያ ባለሙያዎች ያለመኖር መረጃውን እስከ ቀበሌ ድረስ ለማውረድ ክፍተት መኖሩን ጠቅሰው ክፍተቱን ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ኢሳያስ ጠቅሰዋል፡፡

የፌደራልና የክልሎች ግብርና ዘርፍ መስሪያ ቤቶች ፣የምርምር ማዕከላት ፣የሜትሮሎጂ  ኤጄንሲና ሌሎች አጋር ተቋማት ተቀናጅተው የሚሰሩበት መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አመልክተዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ