አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ኢትዮጵያ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ለዜጎቿ ማዳረስ ችላለች Featured

14 Nov 2017
533 times

አዲስ አበባ ህዳር 5/2010 ኢትዮጵያ መሰረታዊ አገልግሎቶችን በአጭር ጊዜ ለዜጎች ማዳረስ መቻሏን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ።

መርሃ ግብሩን የሚደግፉ አጋር ድርጅቶች አራተኛውን ዙር የመሰረታዊ አገልግሎቶች መርሃ ግብር የስራ አፈጻጸም መገምገም ጀምረዋል።

መርሃ ግብሩ በ1998 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን አንድ ዙር ለአራት ዓመታት የሚቆይ ነው።

አገሪቷ ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ በገጠር መንገድና መሰል መሰረታዊ አገልግሎቶች ያስመዘገበቻቸው ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ገለጻ ተደርጓል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንዳሉት  መንግስትና አጋር ድርጅቶች ለመሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የአገልግሎቱ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።

በዚህም አማካይ የዜጎች የመኖር ዕድሜ ከነበረበት 40 በመቶ ወደ 64 በመቶ ከፍ ብሏል።

"ኢትዮጵያ ለዜጎቿ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ በምታደርገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ አልተለያትም" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ድርጅቶቹ በየዙሩ ለሚተገበረው የመሰረታዊ አገልግሎቶች መርሃ ግብር የ600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት ከልማት አጋሮች በበለጠ ለመሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽነት በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት እንደሚመድብም ተናግረዋል።

በጀቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል መደረጉ አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማስቻሉንም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በመሰረታዊ አገልግሎቶች የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች አስቀድማ ማሳካት መቻሏ ለፕሮጀክቶች የሚመደቡ በጀቶች በአግባቡ ስራ ላይ ስለመዋላቸው ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

በክልሎች መካከል ተመሳሳይ የትምህርት፣ የጤና፣ የመንገድና የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች በእኩል ደረጃ ለማዳረስ እንደየክልሎቹ ተጨባጭ ሁኔታ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የልማት አጋሮቹን በመወከል ንግግር ያደረጉት የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ተወካይ ላውራ ፔራሮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋት በተለይም በትምህርትና ጤና ተደራሽነት ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።

ውጤታማ የአስተዳደርና የመረጃ ስርዓት መፍጠር መሰረታዊ አገልግሎቶችን በቀላሉ ለዜጎች ለማዳረስ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሚስ ላውራ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ አኳያ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን በየጊዜው በሚያደርጉት የጋራ ግምገማ ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

የአገሪቷ መንግስት ባለፉት አራት ዓመታት የመሰረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት መርሃ ግብሮች ከፌዴራል እስከ ወረዳ መልካም አፈጻጸም ማሳየቱንም ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በአፋርና በደቡብ ክልሎች የመስክ ምልከታ በማድረግ የፕሮጀክቶቹን ትግበራ ማረጋገጣቸውንም ጠቁመዋል።

በጤናው ዘርፍ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ለማዘመን የተጀመሩ ጥረቶች በሌሎች ዘርፎች ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የኦስትሪያ የልማት ትብብር፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የብሪታኒያ ዓለምአቀፍ ልማት ትብብር፣ የጣሊያን የልማት ትብብር፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የዓለም ባንክ ለመርሃ ግብሩ ድጋፍ የሚያደርጉ አጋር ድርጅቶች ናቸው።

ድርጅቶቹ ለአንድ ዙር 600 ሚሊዮን ዶላር የሚመድቡ ሲሆን፤ በጀቱ ለታለመለት ዓላማ ስለመዋሉ በየስድስት ወሩ ከመንግስት ጋር በሚያደርጉት የጋራ የምክክር መድረክ ይገመግማሉ።

አምስተኛው ዙር የመሰረታዊ አገልግሎቶች መርሃ ግብር ከመጪው ጥር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ