አርዕስተ ዜና

የምርምር ማእከሉ ያቀረበልንን የሰብልና እንስሳት ዝርያዎቸ አምርተን ተጠቃሚ ሆነናል- አርሶ አደሮች

12 Nov 2017
849 times

ደሴ ህዳር 3/2010 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ያስተዋወቃቸውን የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎች በማልማት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

 በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ ቀበሌ 10 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አበበ ''ደይ መረጭ'' በተባለው አረም ምክንያት ላለፉት 25 ዓመታት ምንም ዓይነት ባቄላ አምርተው አያውቁም ነበር፡፡

 በዚህም ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

 "ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማእከል የተገኘውን ''አሸንጌ'' የተባለውን የባቄላ ዝርያ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በመዝራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው" የገለፁት፡፡

 ዘንድሮ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የተሻሻለውን የባቄላ ዝርያ መዝራታቸውንና አዝመራው የተሻለ ቁመና ላይ ስለሚገኝ እስከ 50 ኩንታል ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

 ከ200 በላይ የሚሆኑ የቀበሌው አርሶ አደሮችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል የተሻሻለውን የባቄላ ዝርያ መዝራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

 በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዳዋ ጨፋ ወረዳ የበጤ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በድሩ ኡስማን በበኩላቸው አካባቢው በአቀንጭራ አረም የሚጠቃ በመሆኑ ከአንድ ሄክታር መሬት የሚያገኙት የማሽላ ምርት ከስምንት ኩንታል እንደማይበልጥ ተናግረዋል  ።

 አንዳንዴም ምንም ዓይነት ምርት እንደማያገኙ አስታውሰዋል፡፡

 በመኸር የዘር ወቅት ''ብርሃን'' የተባለውን የማሽላ ዝርያ ተጠቅመው ያለሙት ማሳ በአቀንጭራ አለመጠቃቱንና የተሻለ ፍሬ መያዙን አመልክተዋል፡፡

 በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳ የመነደፈራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ፈንታው አሊ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የተገኘውንና ''ዶርፐር''   የሚል መጠሪያ የተሰጠውን የበግ ዝርያ ከምርምር ማዕከሉ አግኝተው በማዳቀል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 ከማእከሉ  ባገኙዋቸው  በግ ዝርያዎችን በማራባት   በሶስት ዓመት ውስጥ 40 የሚደርሱ በጎች ባለቤት እንድሆን አስችሎኛ ብለዋል ።

 "በኑሮዬም ለውጥ አግኝቻለሁ" የሚሉት አርሶ አደር ፈንታው የተሻሻሉት የበግ ዝርያዎች እድገታቸው ፈጣንና ከፍተኛ የስጋ መጠን ያላቸው ስለሆኑ ገበያ ላይ ጥሩ ዋጋ እንደሚያወጡ አስረድተዋል፡፡

 "ገበያ ላይ ከአካባቢ የበግ ዝርያዎች ከ400 ብር በላይ ብልጫ ስላላቸው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል፡፡

 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ ጋሻው እንዳሉት ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ችግሮች የሚፈቱ  በሰብልና ተፈጥሮ ኃብት ልማት፣ በእንስሳት ልማትና በደን ምርምር የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው ፡፡

 በብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ እውቅና ያገኙ 56 የሰብል ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ማድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

 በተለይ ብርሃን፣ ጎብዬ፣ ሆርማትና አብሽር የተባሉት የማሽላ ዝርያዎች አረም፣ በሽታንና ድርቅን የሚቋቋሙ፣ ከአካባቢው ዝርያ ቀድመው ለምርት የሚደርሱ በመሆናቸው በአርሶ አደሩ ዘንድ ተፈላጊ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

 እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ማዕከሉ በ2009/2010 የምርት ዘመን በሶስቱ ዞኖች ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተሸሻሉ የሰብል ዝርያዎች የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም እስከ 120 ሺህ ኩንታል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 በተጨማሪ የስጋ ምርታቸው የተሻሻሉ፣ በፍጥነት የሚያድጉና ገበያ ላይ የተሸለ ዋጋ የሚያወጡ ከደቡብ አፍሪካ የተገኙ "ዶርፐር" የተባሉ የበግና "ቦር" የተባሉ የፍየል ኮርማዎች ለ77 አርሶ አደሮች ተከፋፍለው 567 የተዳቀሉ ፍየልና በጎች ተወልደዋል፡፡

 በ2009/2010 የምርት ዘመንም 15 ሺህ የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀዋል፡፡

 የስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል ከተቋቋመ 30 ዓመታት እንደሆነው ታውቋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ