አርዕስተ ዜና

በጋምቤላ ክልል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ውስንነት እንዳለበት ተጠቆመ

12 Oct 2017
521 times

ጋምቤላ ጥቅምት 2/2010 በጋምቤላ ክልል የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ውስንነት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

በክልሉ ግብርና ቢሮ አዘጋጅነት በግብርና መካናይዜሽን አሰራር ዙሪያ የሚመክር የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሳታፊዎች እንዳሉት፣ በተለይም የአርሶአደሮችን የአስተራረስ ዘዴ ይቀይራሉ ተብለው የተገዙና በእርዳታ የተገኙ ትራክተሮች ለታለመላቸው አገልግሎት በአግባቡ እየዋሉ አይደሉም።

በእዚህም የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሩ በአግባቡ አለመተዋወቃቸው ለምርታማነት መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል ።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የጎግ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አቡላ ኡሪክ እንዳሉት የአርሶአደሩን የአስተራረስ ዘዴ ይቀየራሉ ተብለው ወደ ክልሉ የገቡ  ትራክተሮች በጥንቃቄ ባለመያዛቸው ለተፈለገው አላማ ሳይውሉ ለብልሽት እየተዳረጉ ነው ።

በተለይም ትራክተሮቹ ከተፈቀደላቸው ሥራ ውጭ ለውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ቁፋሮ እየዋሉ ከመሆኑም በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኑዌር ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያንግ ቾል በበኩላቸው የክልሉን አርሶና ከፊል አርብቶአደሮችን ኑሮ ያሻሽላሉ ተብለው የተገዙ ትራክተሮች ከታለመለት አላማ ውጪ የወረዳ ኃላፊዎች ለባለሀብቶች እንደሚያከራዩና ለብልሽት እየተዳረጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ይህም በክልሉ ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ተጽዕኖ ስላለው የክልሉ መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወረዳዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ በኩል በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡

በዘርፉ የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴም ውስንነት እንዳለበትና ወደፊት ወጣቶችን በማሳተፍ በኩል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

"በተለይም በክልሉ ያለውን ሰፊ የእርሻ መሬት ተጠቅሞ የክልሉን ወጣት ወደ ግብርናው ዘርፍ በማምጣት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን መስራት ይገባል" ብለዋል።

በክልሉ በተለይ የደረሰ ሰብል በሚሰበሰብበት ወቅት የሚስተዋል የምርት ብክነትን ለማስቀረት እየተደረገ ያለው ጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ ለምርት መቀነስ ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ እስማኤል ገለ ናቸው፡፡

"ችግሩን ለመፍታት የክልሉ ግብርና ቢሮም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ይጠይቃል" ያሉት አቶ እስማየል፣ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው አቡፕ በበኩላቸው የክልሉን ሕብረተሰብ ኋላቀር የአስተራረስ ዘዴ ለማሻሻል የመጡ ትራክተሮች ላልተፈለገ ሥራ እየዋሉ መሆናቸውን አምነዋል።

ቢሮው ከእዚህ በፊት ይህን በሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ ሳይወሰድ መቆየቱን ገልጸው፣ በቀጣይ እንደህ አይነት ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል

ወረዳዎች ትራክተሮቹን ለታለመላቸው ዓላማ አንዲውሉ ከማድረግ ባለፈ በጥንቃቄ በመያዝ መጠቀም እንዳለባቸውም ዶክተር ሎው አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ግብርና ቢሮ ከወረዳዎች አቅም በላይ የሆኑ ቴክኒካዊና ሙያዊ ስልጠናዎችን ለመስጠት እንዲሁም ሌሎች መሰል ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ  መሆኑን ዶክተር ሎው አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በክልሉ ለሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ለአርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው ከተከፋፈሉ 32 ትራክተሮች መካከል አምስቱ በብልሽት አገልግሎት አይሰጡም፡፡

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ