አርዕስተ ዜና

የአፍሪካ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለ መጥቷል

12 Oct 2017
1208 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 የአፍሪካ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለ መቀጠሉን በአፍሪካ አገራት የገቢ አሰባሰብ ላይ የተደረገ ጥናት አመለከተ።

የአፍሪካ ታክስ አስተዳድር ፎረም፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንና ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በጥምረት በአህጉሪቷ የ25 ዓመታት የገቢ መጠን መረጃን የያዘ የጥናት ሰነድ ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ ሆኗል።

ከአውሮፓ ሕብረት በተገኘ ድጋፍ በ2017 የታተመውና እ.አ.አ ከ1990-2015 አፍሪካ የነበራትን የገቢ አሰባሰብ የሚተነትነው ሰነድ ከ21 አገራት የተውጣጡ የፋይናንስና ግብር ባለሙያዎች በተገኙበት ነው ይፋ የተደረገው።

የጥናት ሰነዱ ከዚህ በፊት ይጠቀምበት ከነበረው የስምንት አገራት ናሙናን በእጥፍ ጨምሮ የ16 አገራትን መረጃ አጠቃሏል።

በዚህም የእያንዳንዱ አገር የግብር መጠን ለጥቅል ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርት ምጣኔ በአማካይ ያበረከተው ድርሻ እ.አ.አ በ2000 ከነበረው ጋር በመቶኛ ሲሰላ በአማካይ በ5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።

ከ2014 ከነበረው ደግሞ በ2015 በ 0 ነጥብ 4 በመቶ ያደገ ሲሆን በአገራቱ በግብር የተሰበሰበው ገቢ ለጥቅል የአገር ውስጥ ዓመታዊ ምርት ምጣኔ ያበረከተው ድርሻ 19 ነጥብ 1 በመቶ ደርሷል።

በተወሰዱት አገራት የጥናት ውጤት መሰረትም የአፍሪካ የውስጥ ገቢ አሰባሰብ እየተሻሻለ መቀጠሉን ነው ሪፖርቱ ያመለከተው።

ጥናቱ የውስጥ ግብር የሚሰበስብባቸውን ዘርፎች ያነጻጸረ ሲሆን ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ ከምርትና አገልግሎት የተሰበሰበው ግብር መጠን በአማካይ 75 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ አለው።

ከገቢና ከትርፍ የተሰበሰበው የአገራቱ የገቢ መጠንም በአጠቃላይ ከግብር ለተሰበሰበው ገቢ መጠን በአማካይ 32 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛ ድርሻ መያዙን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

እንደየአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ አንጻራዊ ልዩነት ቢኖረውም ከግብር የተሰበሰበው የገቢ መጠን ከግብር ውጪ ካሉ የገቢ ምንጮች ጋር ሲነጻጸር ብልጫ አለው።

ከግብር ውጪ የሚሰበሰብን ገቢ በተመለከተ ገቢው ለጥቅል ዓመታዊ የአገር ውስጥ ምጣኔ ያበረከተው ድርሻ በጥናቱ ከተካተቱ 14 አገራት መካከል የስምንቱ ካለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ እየቀነሰ ሲሆን የስድስቱ ግን ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።

የአገራቱ የገቢ አሰባሰብ መጠን በግብር ስርዓት አወቃቅር አኳያ ከካሪቢያን አገራት ተመሳሳይ ቢሆንም የአፍሪካ ድርሻ ግን ያነሰ መሆኑ ተመልክቷል።

ሪፖርቱ ያካተታቸው አገራት ኬፕ ቨርዴ፣ ካሜሩን፣ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣ ኮት ዲቫር፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሪሸስ፣ ሞሮኮ፣ ኒጀር፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቶጎ፣ ቱኒዚያና ዩጋንዳ ናቸው።

ከአገር ውስጥ ሀብት የሚሰበሰበው የገቢ መጠን መሻሻሉ የአገራቱን የመንግስት አስተዳደርና የንግድ አካባቢ ለማረጋጋት፣ የታክስ አሰባሰብ ፖሊሲና አስተዳደርን ለማጠናከርና ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት ለመላቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ