አርዕስተ ዜና

በቤንች ማጂ ዞን የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅና መዳረሻዎችን ማልማት እንደሚገባ ተመለከተ

12 Oct 2017
536 times

ሚዛን ጥቅምት 2/2010 በቤንች ማጂ ዞን የሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን ማስተዋወቅ ፣መዳረሻዎችን ማልማትና መንከባከብ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የአለም የቱሪዝም ቀን በዓል ትናንት በሸዋ ቤንች ወረዳ የመስህብ ስፍራዎችን በመጎብኘት ተከብሯል፡፡

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አደመ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት በዞኑ የተለያዩ ተፈጥሯዊ ፣ ታሪካዊና ባህላዊ የመስህብ ስፍራዎች ቢኖሩም የመንገዱ ምቹ አለመሆን ጎብኚዎች  በቀላሉ ወደቦታው እንዳይሄዱ ምክንያት ሆኗል፡፡

የጎብኝዎች ማረፊያና መዝናኛ ቦታዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

" በየዓመቱ የቱሪዝም ቀን መከበሩ ሰዎች አካባቢያቸውን እንዲያውቁ ዕድል ይረጥርላቸዋል " ያሉት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ  አቶ ታፈሰ ኢቦ ናቸው፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት የሀገር ውስጥና የወጭ ሀገር ዜጎች እንዲጎበኟቸው ማስተዋወቅ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አቶ ከድር ሼባ የተባሉት የበዓሉ ተሳታፊ በበኩላቸው የአለም የቱሪዝም ቀን በዞን ደረጃ መከበሩ የቱሪዝም ስፍራዎች እንዲለሙ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በዚህም  " መልማት የሚገባቸውን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለይቶ የማልማቱ ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል፡፡

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ሲዝ እንደገለጹት በቤንች ማጂ 64 ሰው ሰራሽ፣ ተፈጥሯና ባህላዊ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ የሁሲቃና የወጀንታ ፍል ውሃ ስፍራዎች፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች የሚጠቀሱ ቢሆንም  የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ላይ አልዋሉም፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን ማልማትና ማበልጸግ ለአካባቢው ብሎም ለሀገሪቱ ዕድገት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት አራት የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት መታቀዱን ያመለከቱት ኃላፊው በሚዛን አማን ከተማ ደረጃቸውን የጠበቁ ሎጂዎችና ሆቴሎች እየተገነቡ መሆናቸው የጎብኝዎችን ቁጥር እንደሚያሳድገውም ጠቅሰዋል፡፡

ባለፈው የበጀት ዓመት የቤንች ማጂ ዞንን የመስህብ ስፍራዎች ከጎበኙ የሃገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች  ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ