አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያን የጥጥ ምርት ከ12 እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ብሄራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ Featured

12 Oct 2017
309 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 የኢትዮጵያን የጥጥ ምርት ከ12 እጥፍ በላይ የሚያሳድግ ብሄራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ሆነ።

ስትራቴጂው ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለ15 ዓመታት በአገሪቱ የሚካሄዱ የጥጥ ልማት እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብር እንዲሁም በጥጥ፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾችና ባለድርሻ አካላትን የሚያስተሳሰር ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራህቱ መለስ እንደተናገሩት በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የወጪ ንግድ አንዱ ነው።

የአገሪቱ የአየር ሁኔታ፣ በመስኖ የመልማት ምቹነትና የመሬት ለምነት ለጥጥ ልማት የተመቸ ቢሆንም የሚጠበቀውን ያህል ምርት እየተገኘ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በጥጥ ሊለማ የሚችል ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ቢኖርም እየለማ ያለው 80 ሺህ ሄክታር ብቻ እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡

የዘርፉን ምቹነት በማሳደግ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች በቂ ግብዓት ለማሟላትና ጥጥ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  ስትራቴጂው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

እንደ ዶክተር መብራህቱ ገለጻ ስትራቴጂው በዘርፉ ከጥጥ አምራች እስከ ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላትን ስለሚያሳትፍና እሴት መጨመር ላይ ትኩረት ስለሚያደርግ በስራ እድል ፈጠራም አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

የጥጥ ምርትና ጥራትን በመጨመር 'በኢትዮጵያ የተሰራ ጥጥ' የሚል መለያ ለመፍጠርም ይሰራል። 

ስትራቴጂው አሁን ለተጀመረው ልማት አጋዥና "በአፍሪካ የቀላል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀዳሚ ለመሆንም ያስችለናል" ብለዋል።

ስትራቴጂው የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ ዘላቂ ማህበራዊና አካባቢያዊ የአመራረት ስርዓትን መዘርጋት፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻና ቅስቀሳ የሚሉ ነጥቦችን ይዟል።

ቀደም ሲል በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተያዘውን ኃላፊነት አቀናጅቶ ሊመራ የሚችልና ተገቢው ስልጣንና ተልዕኮ የተሰጠው መንግስታዊ የሆነ አስተባባሪ ተቋም እንዲመሰረትም ያደርጋል።

ስለ አፈር መከላት፣ የመስኖ ውሃን በቁጠባ መጠቀም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ የተቀናጀ የተባይ መከላከያና ኬሚካሎች አጠቃቀምን በተመለከተም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሀሳቦች አሉት።

ለባለሀብቶች የመሰረተ ልማትና የገንዘብ እገዛ ማቅረብና ለሰፋፊ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች የሚሰጡ ብድሮችና ማበረታቻዎች ዓላማቸውን እንዳይስቱ የሚያስችል የክትትል ስርዓት እንዲዘረጋም ያደርጋል።

ስትራቴጂው ሲተገበር ለጥጥ ልማት የሚውለውን የመሬት ስፋት ከ80 ሺህ ሄክታር በአምስት ዓመት ወደ 250 ሺህ ሄክታር፣ በስትራቴጂው ማብቂያ 15 ዓመት ደግሞ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ያደርሰዋል ተብሎም ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ በ2007/2008 ዓ.ም የሰብል ዘመን 42 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ በማምረት ከአፍሪካ 10ኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን ከ15 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ቀዳሚ የተዳመጠ ጥጥ አቅራቢ ለማድረግ እቅድ ተይዟል።

 

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ