አርዕስተ ዜና

37ኛው የዓለም የምግብ ቀን በመጪው ሣምንት በአዲስ አበባ ይከበራል Featured

12 Oct 2017
271 times

አዲስ አበባ ጥቅምት 2/2010 የዓለም የምግብ ቀን በመጪው ማክሰኞ በአዲስ አበባ እንደሚከበር የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ገለጸ። 

37ኛው የዓለም የምግብ ቀን "በምግብ ዋስትናና ገጠር ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ የስደትን ገጽታ እንቀይር" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚከበረው።  

ሚኒስቴሩ የቀኑን አከባበር አስመልክቶ ከዓለም አቀፉ የምግብና እርሻ ድርጅት /ፋኦ/ ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።   

በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ በሚካሄደው በዚሁ መርሃ ግብር የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የሥራ ውጤቶች ኤግዚቢሽን ይቀርባል። 

በሚኒስቴሩ የገጠር ሥራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳመነ ዳሮታ እንደገለጹት የበዓሉ መከበር በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ለማስገንዘብ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። 

"የዓለምም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ዋነኛ ትኩረት ህገ ወጥ ስደትን ማስቀረት" ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዜጎች በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ መንግሥት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።  

በፌዴራል ደረጃ 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል። 

ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ክልሎች ጋር በመተባበር ወጣቶችን በመስኖ ልማት፣ በዶሮና በከብት እርባታና ማድለብ እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ዘርፍ በማሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጡ የገጠር ወጣቶች የሥራ እድል የተፈጠረ ሲሆን 850 ሺህ የሚጠጉት በግብርና ዘርፍ፣ 696 ሺህ 100ዎቹ ደግሞ ከግብርና ውጪ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

እንደ አቶ ዳመነ ገለጻ በገጠር የተወሰኑ አካባቢዎች የሚከሰተውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ መርሀ ግብር ተቀርጾ ባለፉት 10 ዓመታት በሦስት ምዕራፍ ተከፍሎ ሲተገበር ቆይቷል። 

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የመርሃ ግብሩ አራተኛ ዙር እየተተገበረ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው 8 ሚሊዮን ዜጎች መታቀፋቸውን ጠቁመዋል።

የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተባባሪ ተወካይ አቶ ሀሰን አሊ በበኩላቸው በአገሪቱ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

እስካሁንም በእንስሳት ኃብት ልማትና በግብርና ዘርፍ ከመስራት ባለፈ ድርቅን የሚቋቋም ህብረተሰብና ከባቢ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ በኩል አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።

በአገሪቷ የአነስተኛ ማሳ እርሻ ውጤታማ እንዲሆን ድርጅቱ የፖሊሲ ማማከር አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የጠቀሱት ተወካዩ በበቆሎ ማሳ ላይ በስፋት የታየውን 'የአሜሪካ መጤ ተምች' መከላከል የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የፓናል ውይይቶች፣ ኤግዚቢሽኖችና መሰል መርሀ ግብሮች እንደሚከናወኑ ተገልጿል። 

ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከስደት ተመላሾች ተወካዮች በበዓሉ አከባበር ላይ እንደሚታደሙም ይጠበቃል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ