አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ወደ ቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገቡ ባለሃብቶችን ለመመልመል ዝግጅት እየተደረገ ነው

13 Sep 2017
551 times

ባህርዳር መስከረም 3/2010 የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከማካሄድ ጎን ለጎን በፓርኩ የሚገቡ ባለሃብቶችን የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኪዳኔ ምስክር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ፓርኩን በዚህ ዓመት መጨረሻ ስራ ለማስጀመር የተለያዩ የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴም የፓርኩ ዲዛይን አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰራ የማደረግና የወሰን ማስከበር ስራው መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ለቢሮ፣ ለመመገቢያ፣ ለመኝታ፣ ለመጋዝንና መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ 13 ብሎኮችን የያዘ የካምፕ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

እንዲሁም የ9 ኪሎ ሜትር የአጥር ስራ እየተከናወነ ሲሆን እስከ አሁንም 40 በመቶ የሚሆነው ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የካምፑን የውስጥ ለውስጥ የ10 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ መስመርዝርጋታና ሌሎች የመሰረተ ልማቶችን ከ700 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት ለማከናወን የጨረታ ውል መሰጠቱንና መስከረም መጨረሻ ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በፓርኩ ዙሪያ ከሚገነቡ ሰባት የገጠር የሽግግር ማዕከላትም በሞጣ ማዕከል የአጥር ግንባታ ስራ መጀመሩንና ሌሎች ግንባታዎችን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አቶ ኪዳኔ አስታውቀዋል።

ወደ ፓርኩ ቀድመው ለሚመጡ ባለሃብቶችም ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆኑ ሰባት ሼዶች እንደሚገነቡም አስረድተዋል።

ከግንባታው ጎን ለጎንም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ወደ ፓርኩ ገብተው ማልማት የሚችሉ ባለሃብቶችን ለመመልመል የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስጋ፣ በትክልትና ፍራፍሬ፣ በቅባት እህሎች፣ በመድሃኒት፣ የወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ የማርና ሰም ማቀነባበሪያ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

የፓርኩ መገንባትም የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት አልፎ ለአካባቢው አርሶ አደር የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ2011 ዓ.ም በኋላ በ1000 ሄክታር መሬት ላይ ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም 60 ከፍተኛ 120 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው ታውቋል።

ፓርኩ በዓመት 358 ሺህ ቶን ምርት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገራት ገበያ በማቅረብ በመጀመሪያው ዓመት ከ14 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ያልተጣራ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ