አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በደሴ ከተማ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል

13 Sep 2017
391 times

ደሴ መስከረም 3/2010 በደሴ ከተማ ከኢትዮጵያ ሚሌኒየሙ ማግስት ጀምሮ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል።            

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በከተማዋ በተሰራው የ483 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። 

በደሴ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሰረተ ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌትነት አልታዬ እንዳሉት ለመንገድ ግንባታው ከአንድ ቢሊዮን 750 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።

በገንዘቡ የአስፋልት፣ የጥርጊያ መንገድ፣ የኮብል ስቶን፣ የገረጋንቲና የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች መሰራታቸውን ገልጸው ፣ የዓለም ባንክ ፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት እንዲሁም የከተማዋ አስተዳደር ለመንገዱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የተሰሩት መንገዶች የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ቀደም ሲል መንገድ ያልነበራቸው የከተማዋ አካባቢዎች ለመንገድ ተደራሽ ሆነዋል። 

"የከተማዋ የመንገድ ሽፋን ተደራሽ እየሆነ በመምጣቱ ከ10 ዓመት በፊት የአምቡላንስ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች የማይገባባቸው አካባቢዎች ሳይቀሩ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል" ብለዋል፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በከተማዋ አንድ ዋና መንገድ ብቻ እንደነበር አስታውሰው  ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አማራጮችና አገናኝ መንገዶች በመሰራታቸው የከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ሕብረተሰቡም ለመንገድ ግንባታው ቦታ በመልቀቅና ደጋፊ ግንብ በመገንባት ያሳየው ተሳትፎ ለስራው ውጤታማነት አስተዋጽኦ እንደነበረው አቶ ጌትነት አስታውሰዋል፡፡

በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ቀጠና 2 ነዋሪ አቶ ዘውገ መላኩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመኖሩ የአምቡላንስ ፣ የእሳት አደጋና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢያቸው መድረስ አይችሉም ነበር፡፡

መንገዱ አለመሰራቱ አምሽቶ ለመንቀሳቀስና የማታ ትምህርት ለመከታተል እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የሕብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ጽህፈ ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አድማሴ በሰጡት አስተያየት  በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ብቻ የባጃጅ ትራንስፖርት የሚሰጥባቸው 26 መንገዶች እንዲከፈቱ ተደርገዋል፡፡

በዚህም በከተማ ክልል ውስጥ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ