አርዕስተ ዜና

ባንኩ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ድጋፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው-ዶክተር ካሌብ ወጋሮ Featured

12 Sep 2017
633 times

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ድጋፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የባንኩ የሰባት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶክተር ካሌብ ወጋሮ ገለጹ።       

ዳይሬክተሩ ባንኩ ፈንድ እያደረገ የሚገኘውን የሞምባሳ-ናይሮቢ-አዲስ አበባ አስፋልት መንገድ ግንባታና የኃይል ማስተላለፊያን ፕሮጀክቶች ጎብኝተዋል።

ዶክተር ካሌብ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈንድ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት የጎላ ሚና አላቸው። 

''ባንኩ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በስጦታ በማቅረብ 22 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል'' ነው ያሉት።

ከዚሁ ወስጥ 33 በመቶ ለትራንስፖርት ዘርፍ፣ 19 በመቶ ለኃይል ዘርፍ፣ 16 በመቶ ደግሞ በማህበራዊ ልማት እንዲሁም ለግል ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተለይ ኢትዮጵያን ከኬኒያ ጋር የሚያገናኛት የሞምባሳ -ናይሮቢ-አዲስ አበባ የመንገድ ኮሪደር ግንባታ ተጠቃሽ ነው። 

750 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገዱ ከአገረ ማሪያም እስከ ሞያሌ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን ከአዋሳ እስከ አገረማሪያም ደግሞ ግንባታው እየተከናወነ ነው።    

ግንባታው የኢትዮጵያና ኬኒያ የንግድ ግንኙነትን የሚያጠናክርና የሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ እርስ በእርስ እንዲደጋገፍም ያደርጋል ብለዋል።  

መንገዱ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በቀላሉ የሚያገናኝና የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ውህደት የበለጠ ለማፋጠንም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።   

በኬኒያ በኩል ያለው የመንገዱ ግንበታ የተጠናቀቀ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ያለውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ባንኩ ክትትል እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት። 

በባንኩ ድጋፍ እየተከናወኑ ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲና ኬኒያ እየተዘረጉ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችም በተሻለ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።  

''ይህም ሥራው ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ተጫማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝላትና ኢኮኖሚዋ የሚያድግበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል'' ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድርና እርዳታ በመጠቀም ከአህጉሪቷ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ