አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ከ1 ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ሃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች በገንዘብ ዕጥረት ሳቢያ በተያዘላቸው ጊዜ አልተጀመሩም

12 Aug 2017
570 times

አዲስ አበባ 6/2009  ባለፈው በጀት ዓመት ከአንድ ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ለማካሄድ ቢታቀድም በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ስራው አለመጀመሩ ተገለጸ።

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ለኢዜአ እንደገለጸው ፕሮጀክቶቹ ከውኃ ፣ ከፀሃይ ፣ ከንፋስና ከእንፋሎት ኃይል ለማመንጨት ታስቦ  በባለፈው ዓመት መጨረሻ እና በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ ግንባታቸውን ለማከናወን ታቅዶ ነበር።

ሆኖም የፋይናንስ እጥረትና ዓለም አቀፍ ተቋራጮችን ለማወዳደር የጨረታ ሂደቱ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ  በታቀደው መሰረት  ሊጀመሩ አልቻሉም።።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደገለጹት የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በኦሮሚያ፣በአማራ፣በደቡብ፣ በትግራይና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ለማካሔድ ታቅዶ ነበር።

በነዚሁ ክልሎች አራት  የከርሰ ምድር ወይም እንፋሎት፣አራት የንፋስ እና ሦስት የፀሃይ ኃይል ማመንጫዎች ሥራ ለማስጀመር ነበር የታቀደው።

ዘንድሮም ቢሆን በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ሁሉንም የታቀዱት ፕሮጀክቶችን ማስጀመር አይቻልም ።

በ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በትግራይ ክልል መቀሌ እና ሁመራ እያንዳንዳቸው 100 ሜጋ ዋት ከፀሃይ ኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ።

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አይሻ ሁለት 120 ሜጋ  ዋት የንፋስ ሃይል ማመንጫና  በኦሮሚያ ክልል መተሃራ 100 ሜጋ ዋት የፀሃይ እና በአሉቶ ላንጋኖ የከርሰ ምድር ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሁለት ጉድጓዶች የተጀመሩ ሲሆን ተጨማሪ 24 ጉድጓዶች እስከ ጥር ወር ድረስ ይጀመራሉ።

በተለይ የፀሐይ ሃይል ማመንጫዎች በራስ አቅም የማይቻሉ ስለሆነ  ጥናቱን አጥንቶ፣ግንባታውንም በራሱ አቅም አከናውኖ በቀጣይ 20 ዓመታት ለመንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥ ኩባንያ ለማግኝት ጨረታው ረጅም ጊዜ እንደወሰደ ነው የተገለጸው።

አሁን ግን 18 ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተለይተው በጨረታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ብዙነህ በቀጣይ ስድስት ወራትም ስራው እንደሚጀመር ነው ያስረዱት።

257 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሚጠይቀውና 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው  የአይሻ ቁጥር ሁለትን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመጀመር 85 በመቶ ወጪውን በውጭ ብድር ለማግኘት ቢታቀድም ብድሩ ሊገኝ አለመቻሉን ነው የገለጹት ፡፡

በዚሁ ሳቢያም ስራው መዘግየቱን ያስታወሱት አቶ ብዙነህ ''በአሁን ወቅት ብድሩ ከቻይና ኤግዚም ባንክ ስለተገኘ  ከሐምሌ ወር ጀምሮ በቻይና ዶንግ ፉንግ ኮርፖሬሽን ግንባታው ተጀምሯል ''ብለዋል።

በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መጨረሻ የአገሪቱን የሐይል መጠን 17 ሺህ 347 ሜጋዋት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን አሁን ያለው 4 ሺህ 315 ሜጋ ዋት መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ