አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንዱ የገጠር ወጣቶችን ተጠቃሚ አላደረገም ተባለ Featured

12 Aug 2017
689 times

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2009 መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የመደበውን አስር ቢሊዮን ብር ተንቀሳቃሽ ፈንድ በተለያየ ምክንያት በመዘግየቱ የገጠር ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዳልተቻለ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የገጠር ህዝብ ብዛት በየዓመቱ በአንድ ነጥብ ስምንት በመቶ በማደግ ላይ ሲሆን፤ ዕድሜው ለስራ ዝግጁ የሚሆነው ግን በሁለት ነጥብ ስድስት በመቶ እንደሚጨምር የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ  መረጃ ያስረዳል።

ይህም በገጠር የስራ ፈላጊው ቁጥር ከአጠቃላይ የገጠር ነዋሪው ህዝብ ብልጫ  እንዳለው ያሳያል።

በዚህ የሕዝብ ብዛት ትንበያ መሰረት በሚቀጥሉት ዓመታት በገጠር በአማካይ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የሰው ኃይል በየዓመቱ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈላጊ ይሆናል ተብሎ ይገመታል።

በአሁኑ ወቅትም በርካታ የገጠር ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ በመፍለስ ላይ ናቸው።

ወጣቶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲፈልሱ በበቂ መረጃ ላይ ተመስርተው ባለመሆኑ በሥራ ፍለጋ ጊዜያቸውን ከማባከን ባለፈ የሚፈልጉትን ውጤት እንዳያገኙ እያደረገ ነው።

ይህን ችግር ለመፍታት መንግሥት በ2008 ዓ.ም 'የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ ሰነድ' ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል።

ስትራቴጂው በገጠር የሚኖሩ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች በአካባቢያቸው በቂ ሥራ ተፈጥሮላቸው ከአገሪቷ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዕድገቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 'ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ' የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ ወደ ሥራ ገብቷል።

ይሁን እንጂ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳመነ ዳሮታ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣የገጠር ሥራ ፈላጊ ወጣቶች መንግሥት ከመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በተፈለገው ፍጥነት ተጠቃሚ አልሆኑም። 

በአሁን ወቅት በተንቀሳቃሽ ፈንዱ  ምን ያህል ወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሆኑ የተደራጀ መረጃ አለመኖሩን ጠቁመው፤ በቅርቡ መረጃውን ተጠናክሮ ይፋ እንደሚደረግም  ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዳመነ አንስተዋል።

ገጠርን የአገልግሎት ማዕከል በማድረግ ወጣቶች ባሉበት አካባቢ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግና የወጣቶችን ፍልሰት ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ለዚህም የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ርብርብ እያደረጉ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አቶ ዳመነ ገልጸዋል።

ግብርናና ግብርና ነክ፣ ማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ ግንባታ፣የምግብ ማቀነባበሪያ፣ንግድና ማዕድን ልማት ለወጣቶቹ ሥራ የተፈጠረባቸው ዘርፎች ናቸው።

በ2009 ዓ.ም የፌደራል መንግስት ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ስራ 10 ቢሊዮን ብር መድቦ የነበረ ቢሆንም፤ አማራ፣ትግራይና ድሬዳዋ የተለቀቀላቸውን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠቀሙ ቀሪዎቹ በጀቱን እንዳተጠቀሙበት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ