አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የወጣቶችን ተዘዋዋሪ ፈንድ ከሶስት ክልሎች ውጪ ቀሪዎቹ እየተጠቀሙበት አይደለም ተባለ Featured

12 Aug 2017
538 times

አዲስ አበባ ነሐሴ 6/2009 የወጣቶችን ተዘዋዋሪ ፈንድ ከሶስት ክልሎች ውጪ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ለኢዜአ እንዳሉት አማራ፣ትግራይና ድሬዳዋ የተለቀቀላቸውን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ሲጠቀሙ ቀሪዎቹ በጀቱን አልተጠቀሙበትም።

በ2009 በጀት ዓመት ለወጣቱ ስራ ፈጠራ ከተያዘው 10 ቢሊዮን ብር ውስጥ አራት ቢሊዮን ያህሉ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ ለሁሉም ክልሎች ተመድቧል።

አፋርና ጋምቤላ ክልሎች ከተመደበላቸው ገንዘብ ምንም ያልተጠቀሙ ሲሆን አዲስ አበባም ወደ ካዝናዋ ከገባው 167 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ውስጥ 125 ሚሊዮን ብር ያህሉ አሁንም በካዝናው እንደተቀመጠ ይገኛል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እስከ ሃምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም አለኝ ባለው መረጃ አዲስ አበባ ከድርሻዋ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ መጠቀሟን ቢናገርም የአዲስ አበባ የወጣቶች ማብቃትና ተጠቃሚነት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ አሻግሬ ግን ከባንክ ጋር ውል በመፈራረም ስራ ላይ የዋለው ገንዘብ 15 ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

አማራ ክልል 1 ቢሊዮን 70 ሚሊዮን 827 ሺ 930 ፣ትግራይ ክልል 210 ሚሊዮን 630 ሺ 539 እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ አስተዳድር  21 ሚሊዮን 985 ሺ 886 ብር ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ የተመደበላቸው ሲሆን በጀቱን ሙሉ ሙሉ ተጠቅመዋል።

በዚህም የሶስቱ ክልሎች በጀት አጠቃቀማቸው ጥሩ በመሆኑ የያዝነው ዓመት ተዘዋዋሪ ፈንዱ ከሌሎች ክልሎች ቀድሞ እንደሚለቀቅላቸውም አቶ ሀጂ ተናግረዋል።

ተዘዋዋሪ ፈንዱን በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋሉን  ተከትሎ የወጣቱ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ችግር ከመሆኑ በፊት ሁሉም ክልሎች ገንዘቡን  ለወጣቱ ስራ እድል ፈጠራ ስራዎች እንዲያውሉ ተጠይቀዋል፡፡

ቀሪ ድርሻቸውን ለመውሰድ ቀደም ብለው የወሰዱት ገንዘብ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያሳይ ሪፖርት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዲያቀርቡም ዳይሬክተሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ሃረር፣ደቡብ፣ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ  ክልሎች ገንዘቡን በከፊል ለታለመለት ግብ ያዋሉት ቢሆንም ተዘዋዋሪ ፈንዱን ከመጠቀም አንጻር ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ በፍጥነት እንዲጠቀሙበት አቶ ሀጂ  አሳስበዋል።

መንግስት ከመደበው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ 4 ቢሊዮኑ በተጠናቀቀው በጀት የተከፋፈለ ሲሆን ቀሪው 6 ቢሊዮን ብር ክልሎቹ የወሰዱትን ገንዘብ ባግባቡ ለወጣቱ ማድረሳቸውን ሪፖርት እንዳደረጉ የሚለቀቅ ይሆናል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ