አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ጎጃም ዞን በ700 ሄክታር ኩታገጠም ማሳ ላይ የቀይ ሽንኩርት ልማት እየተካሄደ ነው

17 Jul 2017
1486 times

ደብረ ማርቆስ  ሀምሌ10/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን በተመረጡ ስድስት ወረዳዎች ቀይ ሽንኩርትን ለመጀመሪያ ጊዜ በክረምትና በኩታገጠም የማልማት ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

 በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት አስተባበሪ አቶ ታደሰ ስንቴ  ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ ቀይ ሽንኩርትን በበጋ ወቅት በመስኖ ከማልማት ውጭ በመኸር ዝናብን ተጠቅሞ የማልማት ልምድ የለም፡፡

 ይህ ደግሞ በዞኑ በተለይ ከመስከረም እስከ ጥር ባለው ወቅት ከፍተኛ የቀይ ሽንኩርት ምርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ይህንኑ ክፍተት ለመሙላት ልማቱን በክረምት ወቅት ማካሄድ እንደሚገባ በማመን ለልማቱ ምቹ የአየር ንብረት ያላቸው ወረዳዎችን በባለሙያዎች በመለየት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተያዘው የመኸር ወቅት ወደ ልማት መገባቱን ገልፀዋል፡፡

 በባለሙያዎች እገዛ ልማቱ በመካሄድ ላይ ያለው በሁለት እጁ፣ ጎዛምን፣ ደጀን፣ ባሶሊበን፣ ደብረኤሊያስ እና ማቻከል ወረዳዎች ነው፡፡

 በእነዚሁ ወረዳዎች ደረቃማና ውሃ በማይዝ 700 ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ በኩታገጠም በመካሄድ ላይ ሲሆን ከ900 በላይ አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 ለልማቱም ቀደም ሲል  ከ800 ኪሎ ግራም በላይ የቀይ ሽንኩርት ዘር ለአርሶ አደሩ የተከፋፈለ ሲሆን ከ500 ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽና ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን ጠቁመዋል፡፡

 የጎዛምን ወረዳ የኩራር ቀበሌ ኗሪ ወይዘሮ ትነበብ አስራደ እንዳሉት ከግማሽ ሄክታር በላይ የሚሆን ማሳቸው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በክረምት ቀይ ሽንኩርት መትከላቸውንና ከዚህም ከፍተኛ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

 የባሶሊበን ወረዳ የላም ጌጅ  ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ዘመነምህረት ታምሩ እንዳሉት አንድ ሄክታር በሚሆን ማሳ ቀይ ሽንኩርት ለማልማት አዘጋጅተው በጋራ ስለሚተክሉት ተራቸውን እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

 ''ምርቱም እስከ 4ወር ባለው ጊዜ ስለሚደርስ እኔም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ እንሆናለን ብዬ እጠብቃለሁ'' ብለዋል፡፡

 የጎዛምን ወረዳ የእነራታ ቀበሌ ኗሪ አርሶአደር ሀብታሙ ሳሰኘው እንዳሉት ከዚህ በፊት በበጋ ወቅት በመስኖ ሽንኩርት በማልማት በመጠኑም ቢሆን ሲጠቀሙ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 ''አሁን ደግሞ  በክረምት ወቅት በኩታገጠም  ማሳ ላይ  እንዳለማ እና የበለጠ ተጠቃሚ  እንድሆን ባገኘሁት የባለሙያ ምክር መሰረት ከአንድ  ሄክታር በላይ  ማሳ በማልማት ላይ ነኝ'' ብለዋል፡፡

 ''ምርታማነቱን ለማሳደግም በበጋ ያዘጋጀሁትን ከ10 ኩንታል በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ  ተጠቅሜያለሁ'' ብለዋል፡፡

 በዞኑ በአሁኑ ወቅት በቀይ ሽንኩርት እየለማ ካለው ማሳ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ