አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ለነገ የሚናፈቀው - እግር ኳስ

16 Jul 2017
7015 times

ዳዊት አውነቴ ከኢዜአ

ጊዜው ብዙ አልራቀም፤ በግምት ከሁለትና ሦስት ሳምንታት አያልፍም፤ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ የተለያዩ ዥንጉርጉር ሐሳቦች የተስተናገዱበትና በአፍቃሪያኑ ዘንድ ጎራ አካፍሎ እንዲነጋገሩበት ያደረገ አንድ ጉዳይ ነበር። ይኸውም የአገሪቱ የእግር ኳስ ወቅታዊ አቋም በመፈተሽ እንደው የእግር ኳሳችን ሁኔታ ምን ይመሰላል? በቀጣይስ ምን መሆን  አለበት? የሚለው የመዝናኛው ዘርፍ አንኳር ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ እግር ኳሳችን ተስፋ አስቆራጭና ለኢትዮጵያ እንደማይበጃት ሲገልጹ፤ ሌሎቹ ደግሞ ‘የዘራነውን እየሰበሰብን ነው፤ ምን ሰራንና? ለምንስ ተስፋ እንቆርጣለን?’ በማለት የመከራከሪያ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ። ጥቂቶች ደግሞ "በዘርፉ ምንም ጠብ የሚል ተስፋ ባለመኖሩ ለዘርፉ የሚመደበው በጀት ለሌላ ጉዳዮች መዛወር ይኖርበታል'' ይላሉ። እነዚህም ሙግቶች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን፣ በየመዝናኛ ቤቱ፣ በየአደባባዩ፣ በየትራንስፖርቱና በተለያዩ የመገናኛ ቦታዎች ሲንሸራሸሩ ሁላችንም ታዝበናል የሚል ግምት አለኝ። 

ይህ አይነቱ አስተያየት በየጊዜው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አስደንጋጭና ከባድ ሽንፈት ሲገጥመው የሚሰማ ነው። ኢትዮጵያ በ2019 ካሜሮን ለምታዘጋጀው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጋና፣ የሴራሊዮንና ከኬኒያ ጋር መመደቧ ይታወሳል። ለዚሁ የማጣሪያ ሰኔ 5 ቀን 2009 ዓ.ም የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከጋና አቻዋ ጋር በኩማሲ ስቴዲየም አካሄዳ 5 ለ 0 ተሸንፋ መመለሷ ለስፖርት ወዳዱ ኃዘን የጫረ ክስተት ነበር። ባለፈው ዓመትም በ2017 ጋቦን ላይ ለተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ  የማጣሪያ ጨዋታ በአልጀሪያ አቻዋ   7 ለ 1  መሸነፏ የሚዘነጋ አይደለም።  በአንጻሩ የሰሜንና የምዕራብ አፍሪካ አገሮች በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ አንጸባራቂ ድልን በመጎናጸፍ "እኛም እንዲህ ብንሆን" ብለን እንድንከጅል አድርገውናል።  ( ከጅቡቲ ጋር ተወዳድራ 5 ለ1 በሆነ ውጤት ማሸነፏን አንዘነጋውም። ይህን ግን የጥንካሬ ማሳያ አድርጎ፤ የእግር ኳሳችን ትንሳኤ ነው ብሎ መውሰድ የዋህነት ነው።)

ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ጋር በምድብ ድልድል ስተገናኝ ሽንፈት ከማስተናገዷ በተጨማሪ “ብዙ ግብ ይቆጠርባታል” እያሉ የሚጨነቁ  የስፖርት ቤተሰቦች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ነው።  "የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል" እንደሚባለው ዋልያዎቹ ከእነዚህ አገሮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት በመገናኘት አሳፋሪ ሽንፈት አስተናግደዋል። ይህም  የስፖርት ቤተሰቡ ለአገሪቷ እግር ኳስ ያለው አመኔታ እንዲቀዘቅዝ አድርጓል ። 

በእግር ኳሱ ላይ ብዙዎች ተሰፋ ቆርጠው ከስፖርቱ ራሳቸውን ቢያገሉም ፤  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሠፋ ያለ ውይይት በማድረግ ለችግሩ ሁነኛ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባም የሚከራከሩም አሉ። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ቡድናችን በጋና አቻው ካጋጠመው ሽንፈት በኋላ ፌዴሬሽኑ ምንም አይነት መግለጫ ሆነ አስተያየት ለመገናኛ ብዙኃን አልሰጠም። በተቃራኒው ብሔራዊ ቡድኑ ድል ሲቀናው ሳይውል ሳያድር መግለጫ መስጠቱ የተለመደ ጉዳይ ነው።  ውጤት ሲመጣ  መግለጫ ከመስጠት በተጨማሪ ሽንፈት ሲያጋጥምም ለውይይትና ምክክር  በር መክፈት ይገባል። ምክንያቱም ስህተትን አርሞ  የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራልና። የችግርን መንስኤ ማወቅ ችግሩን  ለማቃለል ቁልፍ ሚና አለው።

በወጣቶች ላይ እምነት አለመጣል

ብሔራዊ  ቡድናችን በየጊዜው አዳዲስና ወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾችን ከማሰለፍ ይልቅ በተመሳሳይ ተጫዋቾች መጠቀም ያዘወትራል። በአገሪቷ ትልቁ የእግር ኳስ የውድድር መድረክ  የፕሪሜርሊግም ይህ ክስተት የተለመደ ነው። ክለቦች ወጣት የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ወደ ክለባቸው ከመቀላቀል ይልቅ እድሜ ጠገብ የሆኑ ተጫዋቾችን  ምርጫቸው አድርገዋል። የሊጉን ዋንጫ በየዓመቱ ከሚያነሳው ክለብ ጀምሮ ላለመውረድ የሚጫወቱት ሁሉ እይታቸውን ከፍተኛ የገንዘብ ዝውውር በሚጠየቁት በእድሜ ጠገቦቹ ላይ ከሆነ ሰነባብቷል። በአገሪቷ ሁለተኛ ሊግ የሚጫዋቱት እንኳ ከተጫዋቾች እድሜ አኳያ ለጤናቸው ሲሉ ስፖርት የሚያዘወትሩ የእግር ኳስ ተጫዋቾች  ጋር ያመሳስላቸዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ከእነዚህ ክለቦች በተውጣጡ እድሜ ጠገብ ተጫዋቾች መገንባቱ  ውጤት እየራቀው ለመምጣቱም በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳል። በመሆኑም ተተኪዎችን በማብቃት ረገድ ብሄራዊ ቡድኑ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

እግር ኳሱ በቂ እውቀት ባላቸው ሃላፊዎች  አለመመራቱ

ከክለቦች ጀምሮ እስክ ፌዴሬሽን ከፍተኛ ኃላፊዎች እግር ኳሱ ግብዓትን አሟልቶ በክህሎት መምራት ላይ ክፍተት ይታይበታል።ይህም  ለእግር ኳሱ መኮላሸት እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል።ከትጥቅ ጀምሮ ኳስና የልምምድ ሜዳዎች በማዘጋጀት የስልጠና መሰረታዊ ቁሳቁሶች እንኳ ሳይቀር ለቡድኑ ለማሟላት የሚከብዳቸው ብዙዎቹ ናቸው። የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንኳ ትጥቅ አልተሟላልንም ብለው ቅሬታ ሲያቀርቡ አስታውሳለሁ። ይሄ የሚመነጨው ደግሞ ለእግር ኳሱ የሚሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የባለሙያ ክፍተት በመኖሩና የፊፋን  ህግና ደንብን  ጠንቅቆ ባለማወቁ ለበርካታ ጊዜ ስህተቶች  ሲፈጠሩ እንደነበር ሁሉም አይዘነጋውም ።

ለአብነትም ወጣት ብሔራዊ ቡድን አባላት ላይ የሚስተዋሉ የእድሜ ስህተቶች እንዲሁም በአዋቂዎች ተጫዋቾች የተመለከቷቸውን ካርዶች መዝግቦ አለመያዝ በተደጋጋሚ  ውጤት እንዲቀነስብንና የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልብን አድርጎናል። ለአብነትም የሴቶች ብሔራዊ ቡድንም (ሉሲዎቹ) ከሁለት ዓመት በፊት አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንዲሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በደብዳቤ ቢያሳውቅም፣ ፌደሬሽኑ ምላሽ ባለመስጠቱ የተፈጠረውን ችግር እናስታውሳለን፤ ለችግሩም በወቅቱ  ኃላፊነቱን የሚወስድ መጥፋቱ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ አድርጎት ነበር።  ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛው ክለቦች ዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማህበር ያስቀምጣቸውን መስፈርቶች  አያሟሉም።  ሁሉም ክለቦች በሚባል ሁኔታ ምቹ የመጫዋቻ ሜዳ  አለማሟላታቸው እንደ ምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።

የተጨዋቾች የልምድ ማጣት 

ብሔራዊ ቡድኑ የተለያዩ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን  በማድረግ ያሉበትን ክፍተቶችና ጠንካራ ጎኑን ለይቶ የማወቅ ችግር ይስተዋልበታል። የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረግም ብሔራዊ ቡድኑ የስነ-ልቦናም ሆነ የአካል ብቃት ደረጃውን  የሚለይበት መንገድ ማግኘት አልቻለም። ዓለም  በእግር ኳሱ ብዙ በተራመደበት በአሁኑ ወቅት፣ ተጫዋቾች እንደሰርግ ጥሪ ቀርቦላቸው ለጨዋታ ተፎካካሪ ለምን? የምንል ከሆነ ብዙ ያላስተዋልናቸው ምስጢሮች አሉ ማለት ነው። በየደረጃው በሚደረጉ ውድድሮች ወጣቶችን በማሳተፍ  እንዲሁ ልምድ እንዲቀስሙና ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱ  ማስቻል ግድ ይላል።

ሥልጠናዎች ወቅቱን ያገናዘቡ አለመሆን

ቀደም ሲል በአገሪቷ  በአጋጣሚም ይሁን  ወይም የእድል እጣ-ፈንታ ሆኖ ድንቅ የእግር ኳስ ተጫዋቾች  ማግኘት ችለን ነበር። በወቅቱ እነዚህ ተጫዋቾች በዘመናዊ ስልጠና ታግዞ  ውጤታማ የሆነ ተጫዋች ለማፍራት እድሉ ዝቅተኛ ነበር ።

በአሁኑ ወቅት እግር ኳስ መዝናኛ ከመሆን አልፎ በዓለም ከፍተኛ የገቢ ማስገኛ ሆኖ እያደገና  የማሸነፍ ስልቱም እየረቀቀ  መጥቷል። ለዚህም ሁሉም አገሮች እንደሌሎች ዘርፎች በትኩረት ሙሉ ጊዜያቸውን በመስጠት ከታች እድሜ ጀምሮ ኮትኩተው ማሳደግ ላይ ይገኛሉ።

በመሆኑም ከሰባትና ስምንት ዓመት ጀምሮ አንድ ተጫዋች  ያለውን ተሰጥኦ  በሳይንሳዊ ስልጠና እየታገዘ  ማሳደግ ካልቻለ ከሌሎች ዓለም አገሮች ጋር መወዳደር አዳጋች ነው። ተጣሞ የተተከለ ችግኝ የለጋ እድሜው ካለፈ በኋላ ለማስተካከል መሞከር ከመስበር ውጭ ውጤት አይኖረውም። በመሆኑም ተጫዋቾቻችን ከህጻንነታቸው ጀምሮ የእግር ኳስ ክህሎት ማሳደግ ካልቻልን በሰላሳ ዓመቱ ወድቀህ ተነሳና ኳሷን ተቆጣጠር ማለት ብትሰበርም ሐኪም ተዘጋጅቶልሃል እንደማለት ነው።

በማንኛውም የስፖርት ዘርፍ ለረጅም ሰዓት ያለድካም በቅልጥፍና ለመስራት የአካል ብቃት እንቅሰቃሴን ማዳበር አስፈላጊ ነው።በእግር ኳስ ውጤታማ ለመሆን እንደሌሎች የስፖርት አይነቶች ተጫዋቾች ለ90 ደቂቃና ከዚያም በላይ ያለድካም የመከላከል፣ የማጥቃት፣ ከተቃራኒ ተጫዋቾች ጋር የመገፋፋትና የመፋተግ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ። ለዚሁ ደግሞ የፍጥነት፣ የጥንካሬ፣ የብርታት ወይም ጽናት፣  ቅልጥፍና እና ሌሎችን እንቅስቃሴዎች ለእግር ኳስ አስፈላጊ ናቸው። በብዙዎች ዘንድ አካል ብቃት ሲባል የሰውነት መግዘፍ፣ የቁመት መርዘም እንዲሁም ሰውነቱ የጡንቻ የፈረጠመ አካል መስሎ የሚታያቸውና ብዙም አስፈላጊ እንዳልሆነ ተደርጎ ሲቆጠር ይታያል።

በመሆኑም የጋና ብሔራዊ ቡድን ብናስተውል ፈጣን እንቅሳቀሴ የታከለበት፣ ጨዋታው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት ተጋጣሚዎቻቸውን የሚያርበድብዱ ተጫዋቾች መሆናቸውንና በአካል ብቃት ከፍተኛ ደረጃ መድረሳቸውን አይተናል። እነዚሁ ተጫዋቾች ግን ተክለ ሰውነታቸውን በማየት የአካል ብቃት እንደሌላቸው የምንቆጥር ትንሽ አይደለንም። ተጫዋቾች  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከታዳጊነት ጀምሮ  በተከታታይ መስራት ይኖርባቸዋል።

የአካል ብቃት ለእግር ኳስ ያለው ሚናን በተመለከተ የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስና የአካል ብቃት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃይለሰማት መርኃጥበብ፤ እግር ኳስና አካል ብቃት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ችግር እንደሚስተዋልበትና ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ሳይታዘቡ አላለፉም።

የአትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸሩ የተክለ-ሰውነታቸው አነስተኛ በመሆኑ ተጫዋቾቹ ከታዳጊነታቸው ጀምሮ ቴክኒካዊ በሆኑት እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ስልጠና ሊሰጥ እንደሚገባ ያጫወቱኝ ደግሞ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር አቶ ይገርማል ንጉሴ ናቸው።

የስነ-ልቦና እና የስነ-ምግብ ባለሙያዎች ለአንድ የእግር ኳስ ቡድን  ውጤታማነት የተለየ ትኩረት እንደሚሻም እንዲሁ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በዘመናዊ እግር ኳስ አንድ ቡድን ውጤታማነት ከእግር ኳስ ዋና አሰልጣኝ በተጨማሪ የአካል ብቃት፣ የስነ- ምግብ፣ የህክምና፣ የስነ-ልቦና ባለሙያዋች  ቁልፍ ሚና አላቸው።

ተጫዋቾች ከጨዋታ በፊት በጨዋታ ጊዜና በኋላ ያላቸው ብቃት ተጠብቆ እንዲቆይ አመጋገብ ከእርፍት፤ ከስነ-ምግብ ባለሙያ የሚሰጥ ስልጠና ወሳኝ መሆኑን አንክሮ ሳይሰጡት አላለፉም። በአገሪቷ ያሉ ክለቦች እነዚህን ሁሉ አሟልተው ስልጠና እየሰጡ ያሉት  ምን ያህሉ እንደሆኑ ቤት ይቁጠረው? ለብሔራዊ ቡድናችንስ  ሁሉ ተሟልቶለታል? እግር ኳሳቸው በአደጉት አገሮች መሰል ስልጠናዎችን እያንዳንዳቸው የተጫዋቾች በየግላቸው የሚያሟላቸው ናቸው።

በከተሞች ማዘውተሪያ ሥፍራ እጥረት 

ስፖርት በተለይም እግር ኳስ  የቴክኖሎጂ እድገት ጋር እያደገ የሚመጣም ቢሆንም፤ በአገራችን ግን በተቃራኒው እየቀነሰ መሆኑ አያጠያይቅም። በተለይ በከተሞች አካባቢ ከመሰረተ ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እየጠፉ መምጣታቸው የስፖርት ቤተሰቡን እያሳሰበው ይገኛል ። ቀደም ሲል የስፖርት ማዘውተሪያ የነበሩት ቦታዎች ለተለያዩ ግንባታዎች በመሰጠታቸው ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማግኘት ከውቅያኖሶች ጠጠር እንደማውጣት ያህል አክብዶታል።

በእርግጥ ታላላቅ ስታዲየሞች እየተገነቡ ቢሆንም በእነዚህ ስታዲየሞች የሚጫወቱ ስፖርተኞችን ለማፍራት  በየሰፈሩ ተጫውተው ተሰጥኦቸውን የሚያሳድጉበት ማዘውተሪያዎች አስፈላጊ መሆናቸው እሙን ነው። የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ከቀድሞው ጋር አነጻጽረው የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በአንድ ወቅት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ብቃት ያላቸው ስፖርተኞችን ለማግኘት አማራጮች የሚወጣበት የማዘውተሪያ ስፍራ እየጠፋ  ነው'' ብለዋል።  መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል። በእርሳቸው ወቅት በርካታ የእግር  ኳስ ተጫዋቾችን  ያፈሩ የማዘውተሪያ ስፍራዎች በየቀዬው እንደነበርም ያስታውሳሉ። "በተለየ መልኩ በፕሮጀክት ታቅፈው ከሚሰለጥኑ ስፖርተኞች የማዘውተሪያ ስፍራ ሊመቻች ይገባል" ሲሉ ይሞግታሉ።

የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በየጊዜው “በመዲናችን ያለውን የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት ለመፍታት እየሰራሁ ነው” ቢልም ጠብ የሚል ውጤት ግን እየታየ አለመሆኑን በየጎዳናው ላይ የሚጫዋቱ  የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ምልክቶች ናቸው።

መፍትሔዎቹስ?

የቀደሙትን ተመልከቱ!

እግር ኳሷ አደጋ ውስጥ የገባባት አውሮፓዊቷ አገር ጀርመን ከችግሯ እንዴት እንደተላቀቀች የሄደችበት መስመር በእውነቱ ከሆነ ለእንደኛ ዓይነቱ አገር ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል። ከአውሮፓና  ከዓለም እግር ኳስ የውድድር መድረኮች በምታደርገው ተሳትፎ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ጀርመን፤ የእግር ኳስ ምሁራንን ጠርታ ምክክር እንዲያደርጉና ለችግሩ መፍትሔ ጀባ እንዲሉ በእጅጉ ተማጽና ነበር። በወቅቱም ምሁራኑ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ በተለይም በታዳጊዎች ላይ እምነት በመጣል መሥራት እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን አቀረቡ።

የሚመለከታቸው አካላትም ወዲያውኑ በታዳጊዎች ላይ ሳይንሳዊ ሥልጠና በመከተል የቡድናቸውን ልዕልና ዳግም ለመቀዳጀት ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዙት። በዚህም ያላሰለሰ ጥረታቸው በጠንካራ ወጣቶች ስብስብ የተዋቀረ ብሔራዊ ቡድን በመገንባት ድሎችን ገና ከጅምሩ መቀዳጀቱን ተያያዙት። በዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሥመ-ጥር ቡድን እንዲሆንና  በተለይም በቅርብ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በዘንድሮው ዓመት ሳይቀር የፊፋ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫን ማንሳት ችለዋል። በተመሳሳይም  ከ20 ዓመት በታች የዓለም ወጣቶች ዋንጫም ሻንፒዎኖች ናቸው። ወጣቶቹ በዋናው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ በመጣ ቁጥር የቡድኑ ጥንካሬም በዛው ልክ ማደጉን ነው የሚጠቀሰው። ልክ እንደ ጀርመን አገራችንም በአግር ኳሱ ውስጥ ተተኪ ወጣቶችን በሥፋት የምታሳትፍ ከሆነ በዘርፉ ላይ ያላት ውጤታማነት አሁን ካለው ደረጃ ማሳደግ ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ በተሳትፎም ይሁን በምስረታ ቀዳሚውን ቦታ ከያዙት አገሮች መካከል አንዷ መሆኗ መቼም አያጠያይቅም። 

የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫን መስራች  እንደመሆኗ መጠን ከውድድሩ መድረክ መራቅ አልነበረባትም። ግን ይሄ ሊሆን አልቻለም። ታዲያ ሳንወሻሽ እግር ኳሳችን መሰረት እንደሌለው ከተማመንን ቀጣዩ ስራ መሰረቱን ለመጣልና ለመውለድ በተግባር መነሳት ይሆናል።

የቀድሞ ዋሊያዎቹ አሰልጣኞች የነበሩት ኢንስትራክተር አብርሐም ተክለሀይማኖትና ሰውነት ቢሻው በአሰልጣኝነት ቆይታቸው በተተኪዎች ላይ መሰረት ያላደረገ መሆኑን በመገንዘባቸውና ችግሩን በመለየታቸው ይመስላል የታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ላይ እየሰሩ ያሉት። ሌሎችም ባለሙያዎችም ሁሉም በእግር ኳሱ ማበርከት  በሚችለው ሁሉ ሃላፊነታቸውን  በመወጣት አሻራቸውን ሊያሳርፉ ይገባል።

የአገሪቷ እግር ኳስ ውድቀት “ብሔራዊ ቡድኑ (ዋሊያዎቹ) ያስመዘገበው ዝቅተኛ የሆነ ውጤት መለኪያ ነው” ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። በመሆኑ የእግር ኳስ ባለድርሻ አካላት ማለትም ክለቦች፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና  የስፖርት ማህበራት ብሎም መገናኛ ብዙሃኑ  ለእግር ኳሳችን ውልደት በቅንጅት በመስራት በስፖርት አፍቃሪውን መካስ ይገባቸዋል ።  

በአጠቃላይ ከታች ጀምረን ለታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሳይንሳዊ ስልጠና ከሰጠን፣  በወጣቶች ላይ እምነት ከጣልን፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ የአካል ብቃት፣ በስነ-ልቦና ስልጠናዎች መሰረታዊ መሆናቸውን ከተገነዘብንና  ከጊዜያዊ ውጤት ይልቅ ለእግር ኳሱ ለውጥ ቅድሚያ ከተሰጠ "በአጭር ጊዜ ውጤታማ ያደርጉናል" የሚል እምነት አለኝ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ