አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የእናት ጥሪ

15 Jul 2017
7158 times

                                                                      መኳንንት ካሳ /አሶሳ ኢዜአ/

 

‹‹ሌቱንም ቀኑንም በሃሳብ ነው የማሳልፈው፡፡ አካሌ እዚህ ቢሆንም ሩሄ ግን እዚያው ልጆቹ ካሉበት ነው፡፡ የሚበላውም የሚጠጣውም ከሰውነቴ ሊጠጋኝ አልቻለም፡፡ በሚነገረው ችግር የተነሳ በሃሳብ አለቅን፡፡››

የተቀመጥንበት የሳር ፍራሽ ላይ ያሉ ቋጠሮዎችን በእጃቸው እያፍተለተሉ፤ አንገታቸውን ያቀረቀሩት  ወይዘሮ ኩሌ ሁሴን የሚተናነቃቸው ሲቃ ድምፃቸውን እየቆራረጠው ንንግራቸውን ቀጠሉ፡፡

‹‹ ልጆቼ በጤና ብቻ አገራችሁ ግቡልኝ፡፡ ምን ይዘን እንምጣ ብላችሁ አታስቡ፡፡ ሃሳባችን በደህና መጥታችሁ አገራችሁ እንድትኖሩ ነው፡፡ ብንሞት እንኳን ከጎናችን ሳትሆኑ መቅረታችሁ ነው፡፡ ስለእናንተ ማሰቡና ጭንቀቱ ጎድቶናል፡፡›› 

የሚተናነቃቸው ሲቃ ገንፍሎ ወጥቶ ፊታቸውን አጠበው፡፡ ሁለት ሴት ልጆቻቸው ሳውዲ አረቢያ የሚገኙት ወይዘሮ ኩሌ ሁሴን ልጆቻቸው ሲደውሉ ምን እንደሚሏቸው ጠይቄያቸው የነገሩኝ ነው፡፡

ልጆቻቸው ሳውዲ አረቢያ ከሄዱ አንደኛዋ አምስት ሌላኛዋ ደግሞ አራት አመት ሞልቷቸዋል፡፡ የሳውዲ አረቢያ መንግስት ካለ ህጋዊ ፍቃድ በሃገሪቷ የሚኖሩ የሌላ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ መመሪያ ካስተላለፈበት ጊዜ አንስቶ እኝህ እናት ልጆቻቸው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መጎትጎታቸውን አላቆሙም፡፡ 

የተወሰነ ሰርተው ለመምጣት በመፈለግ እንጂ አገራቸው መመለሱን ሁሌም እንደሚናፍቁ ልጆቻቸው እንደሚነግሯቸው ወይዘሮ ኩሌ ተናግረዋል፡፡ በሰው ሃገር በሰቀቀን ከመኖር ምንም ይሁን ምን በሃገር መኖርን የሚያህል እንደሌለ እኝህ እናት ገልፀዋል፡፡

ባምባሲ ወረዳ አምባ 49 ቀበሌ የሚኖሩት የወይዘሮ ኩሌ ሁሴን የእናትነት ጥሪ የበርካታ እናቶችም ጥሪ እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ የወለደ አንጀት አይችልም አይደል የሚባለው፡፡ 

ከወይዘሮ ኩሌ መኖሪያ ቤት አቅራቢያ አንዲት ወጣት ከቅርብ ቀናት በፊት ከሳውዲ አረቢያ መመለሷን ስለሰማን በቀበሌው ስራ አስኪያጅ ወጣት አንሻ እንድሪስ መሪነት ወደ መኖሪያ ቤቷ አቀናን፡፡

ከተባለው ቤት ደጃፍ ደረሰን ። አንሻ ደጋግማ ብትጣራም ምላሽ በማጣታችን ወደ ግቢው ዘልቀን ገባን፡፡ በግቢው ከሚገኝ የጎጆ ቤት ሞቅ ያለ ጨዋታ የያዙ ሰዎች ድምጽ ይሰማል፡፡ የመጣችውን ወጣት ‹እንኳን ለሃገርሽ አበቃሽ› ለማለት የተሰበሰበ ዘመድና ጎረቤት ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡

ጎጆ ቤቱን ቀረብ ብለን አንሻ አንድ ሁለቴ እንደተጣራች አንዲት እናት ብቅ ብለው ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከሳውዲ አረቢያ የመጣችው ወጣት እናት ናቸው፡፡ ደስታቸው ከፊታቸው ላይ የሚነበበው እኝህ እናት ልጃቸው ከሳውዲ አረቢያ ከመመለሷ በፊት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

ልጃቸው ወጣት ዘውዴ ጥላሁን ትባላለች፡፡ ሳውዲ አረቢያ የሄደችው በ2005 ዓ.ም ሲሆን በመሃሉ ወደ ሃገሯ መጥታ ዳግመኛ ተመልሳ በመሄድ እስከ ቅርብ ቀናት ድረስ እዛው ቆይታለች፡፡ በህጋዊ መንገድ ከሃገሯ ብትወጣም ከአሰሪዋ ጋር ባለመግባባቷ ከአሰሪዋ ቤት በመጥፋት ካለመኖሪያ ፍቃድ ስትሰራ ቆይታለች፡፡

ካለ መኖሪያ ፍቃድ መኖር ሁሌም ሰቀቀን የሚፈጥር መሆኑን የገለፀችው ወጣቷ ፖሊሶች ቤት ለቤት የሚያደርጉት አሰሳ ተረጋግቶ መኖር የማያስችል እንደሆነ ተናግራለች፡፡

ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ እንደመሆኗ የቤተሰቧን ኑሮ የማሻሻል ኃላፊነቱ የእሷ መሆኑን በማመን ወደ አረብ አገር የወጣቸው ዘውዴ ከአራት ዓመት በላይ የአረብ አገር ቆይታ በኋላ የነበራት ውጥን አለመሳካቱን ተናግራለች፡፡ ዳግም በውጭ ሃገር የምትጥለው ተስፋ እንደሌላት በመግለጽ ከአሁን በኋላ በሃገሯ ሰርታ ለመለወጥ እንዳሰበች አጫውታኛለች፡፡ 

ከእነዘውዴ ቤት ስንወጣ ከቀበሌው ስራ አስኪያጅ ወጣት አንሻ እንድሪስ ጋር ስለዚሁ ስለ አረብ ሀገር ጉዞ ጉዳይ እየተጨዋወትን ስናዘግም እሷም በአባቷ ጥረት ከአረብ አገር ጉዞ መትረፏን ነገረችኝ፡፡ በወቅቱ የአስረኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በአካባቢዋ ወደ አረብ ሃገር የተጓዙ ወጣቶችን በመመልከት የመሄድ ፍላጎት አድሮባት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ነገር ግን አባቷ አጥብቀው ጉዳዩን በመቃወማቸው በወቅቱ ፍላጎቷ ሳይሳካ እንደቀረና ዛሬ ላይ ስታስበው አባቷን እንደምታመሰግን ነገረችኝ፡፡ አንሻ እንድሪስ ትምህርቷን በመቀጠል ከኮሌጅ በዲፕሎማ ተመርቃ ተወልዳ ያደገችበትን አካባቢ እያገለገለች ትገኛለች፡፡

በባምባሲ ወረዳ አምባ 49 ቀበሌ ህገወጥ የሠዎች ዝውውር እንደሚፈፀምባቸው ከተለዩ አካባቢዎች መካከል አንዱ መሆኑን የክልሉ ማህበራዊና ሰራተኛ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ባበክር ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚበዛባቸው አካባቢዎችን በመለየት የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ቁጥጥር ምክር ቤቶችና የቴክኒክ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ኃላፊው አቶ አህመድ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአረብ ሃገራ የተመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከሳውዲ አረቢያ የተመለሱ የክልሉ ነዋሪዎችን ለማቋቋም ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ክልሉ የራሱን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ