አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ሱሰኝነት ከባርነትም በላይ ነው !

13 Jul 2017
4916 times

 ከአማረ ኢታይ (መቀሌ ኢዜአ)

ይህ ታሪክ እውነተኛ ታሪክ ነው።ባለታሪኮቹ እንደወረደ ያጫወቱኝ ታሪክ ።በሱሰኝነት ያሳለፉት ሁኔታና ያጋጠማቸው ፈተና የተረኩበት እውነተኛ ታሪክ ። እኔም የታሪኩን አሳዛኝ ገጽታና የመጨረሻ ውጤቱ በተለይ ለወጣቶች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ  በመሆኑ እንዲህ ከትቤዋለሁ።

እንደ የታሪኩ ባለቤቶች አባባል ሱሰኝነት ከባርነትም በላይ ነው። ወንጀል፣ ባርነት ፣ውርደት፣ነጻነትህን ለሌሎች በገዛ ራስ አሳልፈህ መስጠት፣የእጅ አመል ፣ ውስልትና ፣ በራስ የመተማመን መንፈስ ማጣት፣ድብርት፣የበታችነት ስሜት ማሳደር፣ራስን መጣል፣መገለልና መሰል ችግሮች ያሉበት ነው ሲሉ ባለታሪኮቹ ይገልፁታል ።እስቲ እንከተላቸው።ታሪኩን እንዲህ ያወጉናል።

መቀሌ ከተማ ተወልዶ ያደገ ወጣት ነው።በተሳሳተ መረጃ ወደ ሱሰኝነት ገብቶ ለ14 ዓመታት በተለያዩ ሶሶች ተጠምዶ ቆይቷል።በተጠመደው ሱስ ምክንያት ትምህርቱን ከስምንተኛ ክፍል በላይ መዝለል አልቻለም። ካናቢስ ፣ጫት፣ ሲጃራና የተለያዩ የአልኮል መጠጦችን አንድ ላይ ሲያስኬዳቸው ቆይቷል - ወጣት ናኦድ ግደይ።

ለወጣቱ መልካም የተባሉ ነገሮች ሁሉ የማይጥሙት ነበሩ ። ትምህርት የፋራ ነው።ሰርቶ መብላት እሱም የፋራ ነው።መልካም ስነ ምግባር ምንም አይደለም።እሱን ከሚመስሉ ስድስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን የሱስ አይነቶችን በየተራ እንደ ጉድ ተጠቀምንባቸው ይላል ።

እየዋለ ሲያድር ግን ጉዳቱ እየበረታ መምጣቱ አልቀረም።የገንዘብ እጥረት።የጤና መታወክ። ጭንቀት፣መገለል፣የእጅ አመል ማብዛት፣ የአእምሮ መረበሽና መሰል ህመሞችን አመጣብኝ ይላል ወጣቱ ፤ በዚህ ምክንያትም ከስድስቱ ጓደኞቹ መካከል አንዱን በጭንቀት ብዛት ሲያብድ፣አንዱ ደግሞ የት እንደገባ እስከ አሁን ድረስ አይታወቅም። ሁለቱ ደግሞ ለሞት አደጋ መዳረጋቸው ይናገራል።

ለጋ ወጣቶችን በማታላል የሱሱ ተገዢ እንዲሆኑ ያለመሰልቸት ተንቃሳቅሰናልና ብዙዎችን በሱሱ እንዲጠመዱ አድርገናቸዋል በማለት በቁጭት ይገልጿል።

ሌላው የአደገኛው ሱስ ተገዢ የነበረው ወጣት ተክሊት ዮውሃንስ ይባላል።እሱም ተወልዶ ያደገው በመቀሌ ከተማ ውስጥ ነው።በአካዊንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ከያዘ 13 ዓመታትን አስቆጥሯል - ለስራ አልተጠቀመበትም እንጂ ሲናገር ፊቱን ቅጭም ያደርጋል።በሃሳብ ማእበል ይነጉድና እንደገና ተመልሶ በቁጭት የሱስ አደገኛነትን ለማስረዳት ይሞክራል።

“ሱሰኝነት የተሰረቁ እቃዎችን መደበቅ ፣ መሸጥ ፣መለወጥና ወዲያውኑ ለሱሱ ማስታገሻ ማዋል ያካትታል ሱሰኝነት እስር ቤት ነው ሱሰሽነት ባርነት ነው እንዲያውም ከዚያ በላይም ነው፡፡”  ይለናል።

ወጣት ሳምሶን ዘውዱ ወደ ሱሰኝነት የገባው ገና  በ16 ዓመት ለጋ የወጣትነት ዕድሜው ነበር  ለዘጠኝ ተከታታይ ዓመታት በሱስ ተጠምዶ ቆይቷል። ‘‘ሱስ አይመለከተኝም የሚል ሰው ካለ ተሳስቷል  ሱስ አደጋው ሁሉንም የሚነካ፣ወንጀሉም ሁሉን የሚያጠቃ ነው “ ይላል ወጣት ሳምሶን።

ሱሱ ባመጣብኝ ጣጣ ሁለት ጊዜ ታስሪያለሁ ከምወደው ትምህርትም ተለያይቻለሁ ፤ ለእናቴ የነበረኝ ታላቅ ክብር በፍጹም ጠፍቶ ነበር፤ሌብነት እጅጉን ተጠናውቶኝ ቆይቷል።እናቴ በውድ ዋጋ የገዛቻቸው ጌጣጌጦችን ሳይቀር ሰርቄ በማይረባ ገንዘብ ሽጬ ለሱስ አውዬዋለሁ በማለት በቁጭት ይገልጻል።

ያሳለፈው መጥፎ ሁኔታ ብዙ ውድቀቶችን እንዳደረሰበት እንዲህ በማለት ይገልፀዋል በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩ። አደንዛዠ ቁሶችን በመውሰድ ከትምህርት ጉዞዬን ተሰናከልኩ ። አደንዛዠ እፆችን በዩኒቨርስቲው ጊቢ ውስጥ በድብቅ እየሸጥኩ መደበኛ የመማር ስራዬን ተውኩት፤በርካታ ወጣቶች አበላሸሁ፤በስጨት አለ በሰራው መጥፎ ስራ በእጅጉ መፀፀቱን ገለፀ ።

ወርቃማ ጊዜው፣ቁም ነገር የሚሆንበት ጊዜ፣ስራ የሚይዝበት ጊዜ፣ሃብት ንብረት የሚያፈራበት ጊዜ ሁሉንም በአንዴ ድምጥማጡን አጠፋው።ታዲያ! ይህ ወጣት ቁጭትና ብስጭት ይነሰው!ከሁሉም በላይ ግን ደጋግሞ የምወዳት እናቴን ፣እጅጉን የማፈቅራት እናቴን መጉዳቴና ማሳዘኔ  ለዘላለሙ ይቆጨኛል ሲል ደጋግሞ ይገልጻል ።

ገጠመኙን ከራሱ አልፎ የሌሎች ጓደኞችንም ታሪክ መተረክ ጀመረ።አንድ ወጣት ተወልዶ ያደገው መቀሌ ከተማ ውስጥ ነው።ድፍን ግማሽ እድሜውን ያሳለፈው ከሱስ ጋር ነው። እድሜው 32 ሞልቶታል። መቀሌን እንዴት እንደሆነች ። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቷዋን፣የከተማው የአስፋት መንገዶች ግንባታ፣የዘመናዊ ህንጻዎች ማማር፣የሰው የእለተ እለት አኗኗር፣የኑሮው ሁኔታ አስመልክቶ የሚያውቀው ነገር የለም - በፍጹም።

አንገቱን አቀርቅሮ ከቤት ወደ ሱስ ማስተጋሻው ስፍራ ያቀናል። ከቀኑ ስድስት ሰዓት ተኩል ጀምሮ እዛው የነገር ብቱቶና የሱስ መአት ሲጎትት ውሎ እንደገና ከምሽቱ ሦስትና አራት ሰዓት አከባቢ ሲደርስ አቀርቅሮ እቤቱ ይመለሳል ። ያው! አቀረቅሮ የቀረበለትን እራት ይበላል/ይመገባል/።መተኛት በቃ። ጥዋት ቁርስ በእንቅልፍ ይዘላል።ምሳ ይበላል።እንደገና ተመሳሳይ የህይወት ዑደት ይቀጥላል።ስለ እውነት ለመናገር እስረኛ ነው።ሱስ ከባርነት በላይ ገዝቶታል ይለናል።

በየተራ ያለፈ መጥፎ ታሪካቸውን  በዝርዝር ያጫወቱኝ ስድስት ወጣቶች  ተመሳሳይ ሁኔታ ተጋፍጠዋል ። ሱሰኝነት መግቢያ በሩ እጅግ ሰፊ ነው ።መውጫው ቀዳዳ ግን ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበ ነው።እጅግ አስቸጋሪ ነው ይሉታል።ብዙ ዓመታት ከተጠናወታቸው ሱሰኝነት ለመውጣት ብዙ ብዙ ሙከራዎች አድርጓዋል። የጠፈራቸው ሰንሰለት፣ያሰራቸው ጠላት “ሱሰኝነት” ግን በቀላሉ ሊበጥሱትና ሊላቀቁት ሳይችሉ ብዙ ዓመታትን ተጉዟዋል።

ወጣቶች ምን ጊዜም ቢሆን ከስህተታቸው የሚማሩ ናቸው ። የሚያስተምርና የሚደግፍ አካል ግን ያስፈልጋቸዋል ።  በመቀሌ ከተማ ይህንኑ ድጋፍ የሚሰጥ  አንድ ተቋም ብቅ ብሏል ።

የሱስ ተጠቂዎችን የሚታደግ ተቋም ስሙ “መቋሚያ”ይባላል። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተነሳሽነትና የገንዘብ ድጋፍ በዋናነት የተቋቋመው ይኸው ድርጅት እላይ ታሪካቸውን ምንም ሳይደብቁ “ በኛ ይብቃ! ወጣት ይዳን! “ ብለው የህይወት ታሪካቸውን ላጫወቱን ወጣቶች  ሁሉ ከሱሰኝነት አባዜ ነጻ አውጥቶአቸዋል።

ተቋሙ አንድ የህክምናና የምክር አገልግሎት የሚሰጥበት ማእከል ከፍቶ ሱሶኞችን አንድ ላይ ከሁለት እስከ ሦስት ወራት በማእከሉ ውስጥ እንዲያገግሙ ትምህርትና የህክምና አገልግሎት በመስጠት ይንከባከባቸዋል ።

የሱስ አደገኝነትን፣መንስኤውና ጠንቁ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊ፣ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስመልክቶ በከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎችና የስነ ልቦና ምሁራን አማካኝነት ትምህርት ይሰጣቸዋል ።

ወጣቶቹ ከተጠናወታቸው የሱሰኝነት አባዜ መውጣታቸውን ሲረጋገጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ያደርጋቸዋል ። አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች ከነበረባቸው  ሱሰኝነት  ተላቅቀው የጸረ ሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ሌሎችን ጤናማ መንገድ እንዲከተሉ ለማድረግ የመልካም ስነ ምግባር ምሳሌ ለመሆን በትጋት እያስተማሩ ይገኛሉ ።

ዛሬ ላይ በህይወታቸውና በእለተ ተእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ ታላቅ እፎይታን እንደተጎናጸፉ ይናገራሉ ።ራሳቸውን፣ቤተሰቦቻቸውንና አከባቢያቸውን የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ምክንያት ሆነዋል ። እረፍት አጥታ የነበረችው ነፍሳቸው እፎይ ብላለች። አካላቸው እንደገና መጠንከር ጀምሯዋል።በሱሱ ምክንያት ገርጥተው የነበሩ ፊቶቻቸው መመለስ ጀምረዋል።እንዴት ደስ ይላል።

አደንዥሱስን በመካላከል አገልግሎት ላይ የተሰማራው የመቀሌ ማቆሚያ ማህበረሰብ ልማት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ካልአዩ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርትን ጠቅሰው እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአደንዛዥ እፅ ምክንያት በየደቂቃው ሦስት ሰዎችን ለህልፈት ይዳረጋሉ።ሱሱን የማይጠቀሙ ነገር ግን ከሚጠቀሙ ጋር የሚጠጉና የሚውሉ 10 ሰዎችን በየደቂቃው በተመሳሳይ ሁኔታ ለተለያዩ በሽታዎችና ለአካል ጉዳት ይጋለጣሉ በማለት ያስረዳሉ።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ የሱስ ተጠቂዎች አፍሪካውያን መሆናቸው ነው ይላሉ። በሀገራችን በትክክል የተካሄደ ጥናት ባይኖርም በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለዚህ አደጋ የተጋለጡ ስለመሆናቸው አቶ ኤልያስ ይናገራሉ ።

ድርጅታቸው ከመቀሌና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለት ሚሊዮን ለሚሆኑ ወጣቶች የሱስ አደጋና መፍትሄው ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አመልክቷዋል ።

በማገገሚያው ማእከላቸው ከገቡ እጅግ ሱሰኛ ከነበሩ ወጣቶች መካካል እስከ አሁን ድረስ 350ዎቹ ከነበረባቸው ሱስ ተላቅቀው ነጻ መሆናቸውን አረጋግጠውልናል ።

ሱስ የወንጀል ምንጭ መሆኑን ዓለም አቀፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ ። በተከለከሉና ባልተከለከሉ ሱስ አስያዥ ዕፆችና መድሃኒቶች መንስኤነት የሚፈፀሙ ወንጀሎች ብዙ ናቸው  በዓለማችን 190 ሚሊዮን የአደንዛዥዕፅ ተጠቃሚዎች ይኖራሉ ተብሎም ይገመታል ።

የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ከነዳጅና መኪና አምራች አገሮችና ድርጅቶች በላይ ትርፍ የሚግበሰብስበት መሆኑ ደግሞ ስጋቱን አባብሶታል። በዓመት እስከ 400 ቢሊዮን ዶላር ድረስ የሚታፈስበት መስክ እየሆነ ነው ።

ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸው ኦፔምና ካናቢስ የመሳሰሉ የናርኮቲክ መድሃኒቶችና እፆች ሱስ አስያዥነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል። በድምሩ ሲታይ ሱስ የጤና ፣ የማህበራዊ ፣ ኢኮሚያዊና ፖለቲካዊ ምንጭ መሆኑን አያጠያይቅም ።

ችግሩ በግለሰብ ብቻ ተወስኖ የሚቀርም አይደለም ። አፍራሽ የሆነ ቤተሰባዊ ፣ ማህበረሰባዊ ፣ ሀገራዊ ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ የሚያሚያሳድር በመሆኑ በጋራ ልንከላከለው ይገባል ።

“መቋሚያ “ በመቀሌ የጀመረው ፀረ ሱስ ጥረት መልካም ጅምር ነው ። ግን ደግሞ መልካም ተሞክሮውን ተቀምሮ በመላው አገሪቱ ቢስፋፋ ከሱስ የፀዳ ትውልድ ለማፍራት ይጠቅማልና ይታሰብበት የመቋሚያን መልካም ጅምር በማድነቅ ለወጣቶቻችን መልካሙን ሁሉ ተመኘን።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ