አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ምሩቃን የነገው ስኬት ባለአደራዎች !

11 Jul 2017
8370 times

ምናሴ ያደሳ(መቱ ኢዜአ)

ወቅቱ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎች የረዥም ጊዜ ጥረታቸውን ውጤት የሚያጣጥሙበትና ተቋማቱም በከፍተኛ ጥረት በማስተማር ለውጤት ያበቋቸውን ተማሪዎቻቸውን በደስታ የሚያስመርቁበት ነው፡፡

በአመቱ በሀገሪቱ ከሚገኙ 36 የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 125ሺ 430 በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ደረጃዎች የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ይመረቃሉ፡፡ ከእነዚህም ከ37ሺ630 በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡  ከኢፌድሪ የትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፡፡

በዚህም ሰሞኑን በርካታ የሀገሪቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለያዩ ደማቅ ስነስርአቶች ተማሪዎቻቸውን ማስመረቅ ጀምረዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲም በዚህ ሳምንት ተማሪዎቻቸውን ካስመረቁት አንዱ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲው የኢፌድሪ ፕሬዚደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በክብር እንግድነት በተገኙበት በደማቅ ስነስርአት 1ሺ152 ተማሪዎችን ለአራተኛ ጊዜ ሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም.  በመጀመሪያ ድግሪ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ  ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  የሀገራት ኢኮኖሚም ሆነ ማህበራዊ እድገት ውድቀትና ስኬት ከትምህርት ስርአታቸው ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን የአለምን ታሪክ ዋቢ በማድረግ ተናግረዋል ።

ለማህበረሰባቸው የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሀዊነት ማረጋገጥ የቻሉት ወደ እድገት የሚያደርጉት ጉዞ መጨረሻው ዘላቂና የተሳካ እንደሚሆን ለአብነት ሊወሰዱ የሚችሉ ሀገራትም  በርካታ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ከዚሁ መነሻነት እና ከሀገራዊ እውነታ ጋር የሚጣጣም    በሁሉም ደረጃ የሚተገበር የትምህርት ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ ማድረግ በመጀመሩ በሀገሪቱ ታሪክ  ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል የትምህርት ስርአት ለመዘርጋት ተችሏል፡፡

በዚህም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ በየአመቱ በ100ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን ጨርሰው በመመረቅ በሀገሪቱ  የህዳሴ ጉዞ ላይ ወሳኝ ሚናቸውን እየተጫወቱ እንደሚገኙ ነው ዶክተር ሙላቱ  ያመለከቱት፡፡

የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው የሚወጡ ተማሪዎችም  ሀገሪቱ በአለችበት ደረጃ ከእነሱ የምትፈልገውን ሁሉ በመረዳት በቅንነትና በታማኝነት  ለህዳሴ ጉዞው ዳር መድረስ ወሳኝ ሚናቸውን ሊጫወቱ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“እናንተ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱ ለነደፈችው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት ትልቅ አቅም ናችሁ። በመሆኑም የቀሰማችሁትን ሙያና ክህሎት ለሀገር ልማትና እድገት ለማዋል መትጋት ይጠበቅባችኋል” ብለዋል ዶክተር ሙላቱ ፡፡

ሀገራዊ እቅዱ በዋናነት ሊተገበር የሚችለው ብቁና ተወዳዳሪ በሆነ የሰው ሀይል መሆኑ ሲታይ ደግሞ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውቀትና ክህሎት ይዘው የሚወጡ ተማሪዎች ሀገሪቱ ከድህነት ተላቃ በእድገት ጎዳና የምትራመድ እንድትሆን ለማድረግ  ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲም ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ ሀላፊነት የሚሰማው  እና ብቁ የሆነ ዜጋ በማፍራት ረገድ ይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር በተጨማሪ በጤና መሰረተ ልማት፣ ግብርናን በማዘመን፣ በአካባቢ ጥበቃ በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት መስኮች የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራትን ይበልጥ  በማጠናከር የህዝብ አለኝታነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ በመማር ማስተማር ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ማህበረሰብ አገልግሎት መስኮች ለሚያከናውናቸው ተግባራት የአካባቢው መስተዳድሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አጋርነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አስገንዝበዋል፡፡

በምረቃው ስነስርአት ላይ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ እንዳሉት ተመራቂዎቹ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛውና  በተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብር ከሶስት እስከ አምስት አመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ  ናቸው፡፡

ከተመራቂዎቹ  መካከል 1047 የሚሆኑት በመደበኛው የትምህርት ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ  ሲሆን  ቀሪዎቹ በተከታታይ ትምህርት መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ  ናቸው፡፡ ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ደግሞ 373 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

ዩኒቨርስቲው የአሁኖቹን ጨምሮ ባለፉት አራት አመታት 2ሺ527 ተማሪዎችን ማስመረቁን በስነስርአቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ዩኒቨርስቲው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ በሶስት የትምህርት አይነቶች የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ጀምሯል፡፡የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞችን ቁጥርም ወደ 38 አሳድጓል፡፡

በዩኒቨርስቲው የልማትና ኮርስ ቡድኖችን በማጎልበትና የተማሪዎች የጥናት ቡድኖች በማጠናከር በተሰሩ ስራዎች በአጭር ጊዜ አበረታች ለውጥ ሊመዘገብ መቻሉን ዶክተር ታደሰ አመልክተዋል፡፡

የቤተ ሙከራዎችን በተገቢው መልኩ በማደራጀትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በማሟላት በቀጣዩ የትምህርት ዘመን አልፎ አልፎ ለቤተሙከራ አገልግሎት ወደ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎችን የመላክ አሰራር ለማስቀረት የተጠናከረ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

በዘንድሮው አመት ሁሉም የቤተ ሙከራዎች የኢንተርኔት አገልግሎት የተዘረጋላቸው ሲሆን ቤተ-መጽሀፍቶችንም በተለያዩ ስብስቦች በማጠናከር በአሁኑ ወቅት ለ22 ሰዓታት ክፍት ሆነው ተማሪዎቻቸውን እንዲያገለግሉ ተደርጓል፡፡

ዩኒቨርስቲው ለአካል ጉዳተኞች፣ከታዳጊ ክልልና አርብቶ አደር አካባቢዎች ለመጡ ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርግና ለአጠቃላይ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የእንግልዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ፕሮግራም በማዘጋጀት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እየሰራ ነው፡፡

ለሴት ተማሪዎች ከሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት በተጨማሪ በዩኒቨርስቲው አብያተ መጻህፍት ለሴቶች የተለየ የማጥኛ ክፍል በመፍጠር ድጋፍ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ በየአመቱም ጥሩ ውጤት ያመጡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና እየተሰጠ ነው፡፡

እንደ ዶክተር ታደሰ ሀብታሙ ማብራሪያ ዩኒቨርስቲው በሁሉም ዘርፎች እያደረገ ባለው ጥረት የተማሪዎች የመውደቅ መጠን በዚህ አመት ወደ 1.7 ከመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

የመቱ ዩኒቨርስቲ ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ማህበረሰብ አገልግሎት መስኮች ከአካባቢው መስተዳድሮችና ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር  በተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ማላመድ፣ በአካባቢ ጥበቃ በወጣቶች ስራ እድል ፈጠራና በሌሎችም መስኮች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በአካባቢ ጥበቃ ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ከሀገር ውስጥ ዩኒቨርስቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር የጋራ ፕሮጄክት በመቅረጽ በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በጋራ እየሰራ ሲሆን በዚህ አመትም በዩኒቨርስቲዉ ምሁራን የቀረቡ 58 የጥናትና ምርምር ፕሮፖዛሎች ጸድቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በሁሉም መስኮች እያከናወናቸው ባሉት ተግባራት በ2012 ከሀገሪቱ ምርጥ አስር ዩኒቨርስቲዎች አንዱ ሆኖ ለመውጣት ግብ ጥሎ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡት ተመራቂዎች መካከል  በመካኒካል ምህንድስና ትምህርት የተመረቀው ግርማ ሻሾ እንዳለው ሀገሪቱ እያስመዘገበች ባለው ፈጣን እድገት እና የቴክኖሎጂ አቅሟም እያደገ ባለበት   ወቅት መመረቁ  የቀሰመውን ሙያ በሚገባ በመጠቀም ለሀገሪቱ እድገት የሚጠበቅበትን ለመወጣት አነሳስቶታል፡፡

በግሌም ይሁን በተቋማት በመቀጠር የያዝኩትን ሙያ በስራ ላይ ለማዋል ብዙ አማራጮች እንዳሉኝ ይሰማኛል” ያለው ተመራቂው በአጠቃላይ ልማቱ ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ከወዲሁ መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡

በጎልማሶች ትምህርትና ማህበረሰብ ልማት  የተመረቀው ካሳሁን ሀይለማሪያም በበኩሉ በዩኒቨርስቲ ቆይታው የቀሰመውን እውቀት በአፋጣኝ ወደ ተግባር በመቀየር ከወጣቱ በተጨማሪ ጎልማሶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቅማቸውን የማሳደግ ስራ ለመስራት ተዘጋጅቷል፡፡

“ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ ነው ያለችው በመሆኑም ወጣቱ በዩኒቨርስቲ ቆይታው በፈጣን ልማቱ ውስጥ በደረጃው የሚጠበቅበትን ወሳኝ ሚና እንዲወጣ ትምህርትና ትምህርት ብቻ አላማው በማድረግ  ብቁና ተወዳዳሪ  ሊያደርገው የሚችል እውቀት  ለመጨበጥ ጥረት ማድረግ አለበት” ብሏል፡፡

በዩኒቨርስቲው ምረቃ ስነስርአት ላይ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች የተዘጋጀላቸውን ሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማት ከእለቱ የክብር እንግዳ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እና ከመቱ ዩኒቨርስቲ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ አስቴር ማሞ እጅ ተቀብለዋል፡፡

 የመቱ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት በ38 ቅድመ ምረቃና 3 ድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች 11 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በመደበኛውና ተከታታይ መርሀግብር  በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማጠናቀቂያ ላይም በሁሉም ፕሮግራሞች የቅበላ አቅሙን ከ23 ሺህ በላይ ለማድረስ  እቅድ ነድፎ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ