አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የበጎ ፈቃድ አገልሎት - የመልካምነት ነጸብራቅ

09 Jul 2017
3738 times

የፀዳወረቅ ታደለ (ኢዜአ)

በየዓመቱ ክረምት ሲመጣ ከዩኒቨርሲቲ ወደ ቤተሰቦቻቸው ለዕረፍት የተመለሱ፣ በወጣት ማህበራት የታቀፉ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ወጣቶች በየአካባቢያቸው ተሰባስበው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ። ይህ ደግሞ በአገራችን የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል።

ወጣቶቹ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ፣ ደም ልገሳ ፣ የአካባቢ ልማትና ችግኝ ተከላ በማካሄድ እንዲሁም የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዙሪያ የተለያዩ አገልግሎቶችን በነፃ ይሰጣሉ። በጎዳና ላይ ላሉ ወጣቶች ምክርና ስልጠና ፣ አረጋዊያንን መርዳት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዙሪያ ግንዛቤ የመስጠት ተግባራትንም ያከናውናሉ።

የዘንድሮ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "በተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ህዳሴያችንን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ሀሳብ የዝግጅት እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ ቆይተዋል።

ለአብነት በመዲናችን የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት የተደረገውን ዝግጅት መመልከት ይቻላል። ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው በክረምት የሚያስተምሩ ወጣቶች አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታዎች ማመቻቸታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ዳግማዊ ሚኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ፣ መስከረም አፀደ ህጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ እና ምስራቅ ጎህ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ነው የገለጹት። በቂ የሆነ የመማሪያ ክፍሎች ማዘጋጀት፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማሳለጥ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች ማሟላት በዝግጅት ምዕራፉ የተከናወኑ ተግባራት ናቸው።

ማስታወቂያ በየቦታው በመለጠፍና በራሪ ወረቀቶችን በመበተን ተማሪዎችና ወላጆች መረጃው እንዲደርሳቸውና ልጆች ለክረምት ትምህርት ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡም እንቅስቃሴዎች ተደርጓል። አቅም ለሌላቸው ልጆች ደግሞ አልባሳትን ጨምሮ የመማሪያ ቁሳቁሶችን በፈቃደኝነት መሰባሰቡንና ለማከፋፈልም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ነው የነገሩን።

በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከተመዘገቡ ወጣቶች ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት ንጋቱ ተሻለ አንዱ ነው። ''በየዓመቱ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ነው የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው ዘንድሮም በዚሁ ዓይነት ተግባር በማሳለፍ ተተኪ ትውልዶችን በማብቃት ረገድ የድርሻዬን እወጣለሁ'' ነበር ያለው።

የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ባሉበት በዚህ ወቅትም ተመላሾችን የመቀበልና እነርሱ የሚፈልጉትን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያግዙበት ሁኔታም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተካቷል። 

በዚህም ከ500 የሚበልጡ የክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሳዑዲ ተመላሾችን በመቀበል ላይ ይገኛሉ። ወጣቶቹ በቀንና በማታ መርሃ-ግብር ተከፋፍለው ተመላሾችን በመቀበል፣ የስልክ አገልግሎት በመስጠት፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እስከሚገናኙ የሚያርፉበት መጠለያ በማዘጋጀት፣ ሻንጣዎቻቸውን በማፈላለግና በማገዝ ብሎም የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራን እያከናወኑ ነው።

ያነጋገርናቸው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለወገኖቻቸው በሚያደርጉት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት። የእረፍት ጊዚያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ይህንን በመሰለ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያሳለፉ በመሆናቸው ለህብረተሰቡ ከሚሰጡት ጠቀሜታ ባሻገር የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውንም ይገልጻሉ።

ወጣት ኪሮስ ኪዳነማርያምና ወጣት ፍሬወይኒ አበባው በግልና በመንግስት ስራ የተሰማሩ ወጣቶች ናቸው። ወጣቶቹ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘወትር ክረምት በመጣ ቁጥር ተሳታፊ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ከስራ ሰዓት ውጪ በሚኖራቸው የዕረፍት ጊዜ ከሳዑዲ ተመላሾችን በመቀበል ላይ ናቸው፤ ይሄ ደግሞ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አባል ወጣት ሕብስቱ አራጋውና ወጣት ይመር ተሾመም እንዲሁ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ መሆኑን ይናገራሉ።

ወጣት ይመር ”በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎችን ተቀባይ በመሆኔ የተለየ ስሜት ፈጥሮብኛል፤ መረዳዳታችንንም በግልጽ የሚያሳይ ነው'' ብሏል።

ወጣት ህብስቱም ከወጣት ይመር ጋር ተመሳሳይ ስሜት እንዳሳደረባት ገልፆ ፤ በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ ያልሆኑ ወጣቶች የዕረፍት ጊዜያቸውን በጎ ተግባር በማከናወን የህሊና ዕርካታ እንዲያገኙ ጥሪ አቅርቧል።

ከሳዑዲ ተመላሽ ዜጎችም በወጣቶቹ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ወጣቶቹ ያለምንም ክፍያ በበጎ ፈቃድ የሚያደርጉላቸው እገዛ በገንዘብ ቢተመን ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ነውም ይላሉ። ከወጪ ባለፈም ያጋጥም የነበረውን እንግልት ማስቀረቱን ይመሰክራሉ። የተመላሾቹን ሻንጣ መፈለግና የጠፋ ካለም የሚመለከተው አካል ጋር በመሄድ መፍትሄ እንዲያገኙ ትብብር ያደርጋሉ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፈው ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶቹ በበጎ ፈቃድ ያከናወኑት ተግባር በገንዘብ ሲተመን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ነው። በበጎ ፈቃድ የክረምት ትምህርት አገልግሎት ዘርፍ 1 ሺ 375  ወጣቶች ተሳትፈው ፤ 78 ሺ ተማሪዎችን አስተምረዋል። በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ደግሞ 31 ሺ ተማሪዎች ሥልጠና ማግኘታቸውንም ነው መረጃዎቹ የሚገልፁት። 

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን በዘንድሮ ክረምት 900 ሺ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያሳትፋል። የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳት ወጣት አባይነህ አስማረ እንደሚለው፤ በአዲስ አበባ አስተዳደር ወጣቶቹ በክረምቱ በተለያዩ መስኮች አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል። በዘንድሮው የበጎ ፈቃድ የሚሰጠው አገልግሎት 50 ሚሊዮን ብር እንደሚገመትም አብራርቷል።

በዚሁ የበጎ ፈቃድ ስራ ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣቱ 2 ሺ 200 ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጡም ነው የተናገረው። በዚህም በከተማዋ በሚገኙ 100 ትምህርት ቤቶች 85 ሺ ለሚደርሱ ተማሪዎች የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም አብራርቷል።    

በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ደግሞ 50 ሺ ተማሪዎች ስልጠና እንደሚያገኙ የተናገረው ወጣት አባይነህ፤ አቅም ለሌላቸው 10 ሺ ህጻናትም የመማሪያ ቁሳቁስና አልባሳት ማሟላታቸውንም ገልጿል። 

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ ስድስት ሺ ወጣቶች በደም ልገሳ የሚሳተፉ ሲሆን፤ 100 ሺ ወጣቶች ደግሞ 200 ሺ ችግኞችን ይተክላሉ። አንድ ሺ 500 ወጣቶች በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትና በትራፊክ ደህንነትና በአካባቢ ልማትና ጽዳት ተግባር ተሳትፈው በመዲናዋ በተመረጡ ቦታዎች 35 ሺ ሜትር ኪዩብ ቆሻሻን ያስወግዳሉ። ከ20 ሺ በላይ ወጣቶች ደግሞ ጤናና ሰብዓዊ አገልግሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

ሦስት መቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም በዘርፉ ስልጠና እንደሚሰጡ ነው ወጣት አባይነህ የተናገረው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን በበኩሉ ዘንድሮ በመላው አገሪቷ ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች በሚፈልጉት መስክ በቀላሉ እንዲሰማሩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ተናግሯል።

የፌዴሬሽኖቹ ፕሬዚዳንቶች ትምህርት ቤቶች ለክረምት ነፃ ትምህርት ተማሪዎችን ከመመዝገብ ጀምሮ እንደተባበሩዋቸው ነው የሚገልጸው። ትብብራቸው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።

በወጣቶቹ የሚሰጠው የክረምት ትምህርት ሐምሌ 03 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ ይጀመራል። ሁሉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በዚሁ እለት እንደሚጀመሩም ተገልጿል።

ባለፈው ዓመት የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት "እኛ ወጣቶች የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ከዳር ለማድረስ በዕውቀታችንና በጉልበታችን እንተጋለን" በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወሳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ