አርዕስተ ዜና

“ታሪክና ቅርስን አስጠብቆ የማቆየት መልካም ጉዞ”

09 Jul 2017
5894 times

                     ነጻነት አብርሃም (ኢዜአ)

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በተፈጥሮ ሃብትና ቅርስን ጠብቆ በማቆየት በዓለም በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ከሶስት ሺ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ጥንታዊ ስልጣኔና ታሪክ ባለቤት መሆኗንም ድርሳናት ይጠቅሳሉ።

ይህቺ ቀደምት አገር በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አሏት፡፡  ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቀው የቆዩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን በአግባቡ መንከባከብና መያዝ የሁሉም ዜጋ ኃለፊነትና ግዴታ ነው። የታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ባለቤት መሆን ለብቻው የሚያኮራ ባለመሆኑ ባለአደራው ትውልዱ ያለፈውን መልካም ጉዞ ማስቀጠል ይጠበቅበታል።

ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስ እና ባህል ድርጅት /ዩኒስኮ/ በተገኘ መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ 28 የሚሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች፡፡ ከእነዚህ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ታሪካዊ ቅርሶች መካከል አንዱ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነው።

በአገሪቷ ከሚገኙ አንጋፋ ብሔራዊ ፓርኮች መካከል አንዱ የሆነው ይህው ፓርክ፤ በውስጡ እንደ ዋልያ አይቤክስ፣ ሰሜን ቀበሮ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና የመሳሰሉትን ብርቅዬ እንስሳትን አቅፎ ይዟል፡፡  ፓርኩ እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ቢመዘገብም፣ በአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፉ በመጡ ሕገ ወጥ ሰፈራዎች፣ የሞፈር ዘመት እርሻና ልቅ ግጦሽ ህልውናው አደጋ ውስጥ ወድቆ ቆይቷል፡፡

ለዚህም ነው ዩኒስኮ ላለፉት 21 ዓመታት ፓርኩን በአደጋ መዝገብ ውስጥ አስፍሮ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግለት ሲያሳስብ የከረመው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት የዋልያና ቀይ ቀበሮ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መመናመን ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድረጎት ቆይቷል፡፡ እነዚህን እና ሌሎች አሳሳቢ ጉዳዮችን የተገነዘበው ዩኒስኮ እ.ኤ.አ 1996 ባካሄደው 20ኛው መደበኛ ስብሰባ ፓርኩን ለመታደግ በማለም በአደጋ መዝገብ አስፍሮታል፡፡

ይህንን ታሪካዊ ፓርክ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ ለማስወጣትና ወደቀድሞ ታሪኩ ለመመለስ ምን ተሰርቷል? የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ፓርኩን በአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር ካደረገ በኋላ የፌዴራል መንግስት፣  የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የአካባቢው አስዳደርና ነዋሪዎች  ተቀናጅተው ፓርኩን ወደነበረበት ደረጃ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አሁንም ጥረቱ እንደቀጠለ ነው። በተለይ በአካባቢው ለሚኖሩ ማህበረሰቦች በተሰጠው ሰፊና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባር በማህበረሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ተችሏል፡፡ ፓርኩን ከሰዎች ለመጠበቅ እንዲያስችልም ፓርኩን አቋርጦ እንዲያልፍ ተገንብቶ የነበረው መንገድ በሌላ አማራጭ መንገድ እንዲተካ ተደርጓል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም ጉዳዩን አስመልክተው እንደገለጹት፤ ህዝብና መንግስት ፓርኩ እንዲጠበቅና ለቱሪስት መስህብ የተሻለ ገጽታ እንዲኖረው በማድረግ በኩል ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል።

''በፓርኩ ውስጥ ሰፍረው የነበሩ የግጭ መንደር ሰዎች እንዲወጡና እነርሱ በሚመርጡት ቦታ ላይ መንደር እንዲመሰርቱ የማድረግ ስራ ተከናውኗል። መንግስትም በፓርኩ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች 158 ሚሊዮን ብር ካሳ ሯፍሏል'' ይላሉ።

በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ለተነሺዎች ወደ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቦታ መስጠቱን ይገልጻሉ። በዚህም 166 አባወራዎች ከፓርኩ ወጥተው ደባርቅ ከተማ  መኖሪያ ቤት ተሰርቶላቸው እንዲሰፍሩ መደረጉን ነው ያመለከቱት።

የአማራ ብሄራዊ ክልል አካባቢ፣ ደን፣ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ እንደሚሉት፤ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት መንግስትና ህብረተሰቡ ተቀናጅቶ የፓርኩን ሁለንተናዊ ደህንነት ለመመለስ ብርቱ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በመሆኑም በተከናወኑ ተግባራት የፓርኩን ክልል ከነበረበት 136 ኪሎ ሜትር ስኩየር ወደ 412 ኪሎ ሜትር ስኩየር ማስፋት መቻሉን ነው የጠቆሙት። እንዲሁም ለዱር እንስሳቱ በተደረገው ጥበቃም የዋልያዎቹ ቁጥር ከ150 ወደ አንድ ሺ፤ የቀይ ቀበሮዎችን ቁጥር ደግሞ ከ40 ወደ 100 ማሳደግ ተችሏል።

ይህ ታሪክና ቅርስን አስጠብቆ የማቆየት መልካም ጉዞ ተምሳሌት ነው። ለዚህም ነው ዩኔስኮ ፓርኩ የሚገኝበትን ሁኔታና ወደ ነበረበት ለመመለስ የተደረጉ ጥረቶችን የቃኘው።

ዩኔስኮ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ያለበትን ተጨባጭ ለውጥ በመገንዘብም ከአደጋ መዝገብ ውስጥ አውጥቶታል። ድርጅቱ ላለፉት 21 ዓመታት በፓርኩ ላይ ያበራውን ቀይ መብራት አጥፍቷል።

የአለም ቅርስ ኮሚቴ በፖላንድ ክራኮዎ ባካሄደው የዓለም ባህላዊ ቅርስ ኮሚቴ 41ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በፓርኩ አያያዝና አስተዳደር ዙሪያ ውጤት መምጣቱን በመገምገም ፓርኩ አደጋ ውስጥ ከሚገኙ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ ወስኗል። ይህ ውሳኔ ሊመጣ የቻለው ባለፉት ዓመታት በተከናወነ  የቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ስራ ነው። በዚህም የዓለም ባህላዊ ቅርስ ሃያ አንዱም የኮሚቴው አገሮች በውሳኔው በሙሉ ድምጽ በመስማማት ፓርኩ ከአደጋ መዝገብ ውስጥ እንዲሰረዝ አድርገዋል።

ኮሚቴው ኢትዮጵያ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው መንገድ የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ተለዋጭ መንገድ ለመገንባት፣ ልቅ ግጦሽ እና የጎብኝዎችን ተፅዕኖ ለመቀነስ ያሳየችው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጿል። በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ እንደ ዋልያ እና ጭላዳ ዝንጀሮ ያሉ ብርቅዬ የዱር እንሳትን ጠብቆ በማቆየት ረገድም መልካም ስራ መከናወኑን በመጥቀስ አድንቋል።

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የዋልያና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት ብቸኛ መገኛ በመሆኑ በየዓመቱ እስከ 15 ሺ የሚደርሱ የውጪ ሀገር ቱሪስቶች እንደሚጎበኙት ይነገርለታል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ፓርኩን የጎበኘችው የሲኤንኤን ዘጋቢ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን "የሰሜን ተራራ ውብ ተፈጥሮ፣ ትንፋሽ ቀጥ የሚያደርግና ሁሉም ሰው በህይወት ዘመኑ ሊጎበኘው የሚገባ ስፍራ ነው" ስትል በመደነቅ ስሜት ገልጻዋለች። 

እንደነዚህ ዓይነት የአገሪቷን ታሪካዊና የቱሪስት መስህብ የሆኑ ቅርሶችን የመጠበቅና የማልማት ስራ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆን ይኖበታል። ስለሆነም በሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ የተገኘው ውጤት ሌሎች አካባቢዎች ተሞክሮ ስለሚንሆን ማስፋት ተገቢ ነው።

ከዚህ አኳያ በየአካባቢው የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግና አመለካከት የመቀየር ስራ መከናወን ይኖርታል። በዚህም የቅርስና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። የአገሪቷ ጥንታዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ ሀብቶች ተጠብቀው  እንዲቆዩ በማድረግ በኩል የተለያዩ  ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥና የማስፋት ስራ ማከናወን ይኖርባቸዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ