አርዕስተ ዜና

በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የግንባታ ባለሙያዎችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው

19 Jun 2017
557 times

አዲስ አበባ ሰኔ 12/2009 በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የግንባታ ባለሙያዎችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር የአቅም ግንባታ ስራ እያከናወነ መሆኑን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።

 ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመቀሌ፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች በግንባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ለአምስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና በመስጠት ላይ ነው።

 በሚኒስቴሩ የባለሙያዎችና ኩባንያዎች አቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢያሱ ማርቆስ እንደተናገሩት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በሀብት አጠቃቀምና፣ በድርጅት አስተዳደር ከፍተኛ ችግሮች ይታይባቸዋል።

 በጥናቱ ግኝት መሰረትም ባለሙያዎቹ ያለባቸውን የዕውቀት ክፍተት በመለየት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

 የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ መንግስት የ10 ዓመት የአቅም ግንባታ ማዕቀፍ ፕሮግራም ቀርጾ በመስራት ላይ ነው ብለዋል አቶ ኢያሱ።

 ባለፉት ዓመታት በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ባለሙያዎችን ብቃትና ክህሎት ለማጎልበት በተሰሩ ስራዎች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል ነው ያሉት።

 ለባለሙያዎች የተሰጡ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ በማመቻቸት፣ ከዓለም አቀፍ መድረኮች የተሻሉ ተሞክሮዎችን እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

 በአሁኑ ወቅት ከ40 በላይ የጥራት ስራ አመራር ደረጃ ያገኙ ባለሙያዎች አሉ ያሉት አቶ ኢያሱ የባለሙያዎቹ ቁጥር ከአገሪቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ እድገት ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ቁጥሩን ለማሳደግ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 በቀጣይም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት፣ አሰራሮችን የማሻሻልና የማዘመን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ