በአዲስ አበባ በሁለት ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ጫማ ተያዘ

19 Jun 2017
478 times

አዲስ አበባ  ሰኔ 12/2009 በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በሁለት ግለሰቦች በህገ-ወጥ መንገድ በመኖሪያ ቤት የተከማቸ ጫማ በኅብረተሰቡ ጥቆማ ተያዘ።

በክፍለ ከተማው ወረዳ ሶስት በሁለት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በተለያዩ ጊዜያት በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቸ ጫማ በኅብረተሰቡ ጥቆማ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የኮልፌቀራኒዮ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እና ፖሊስ ትብብር ዛሬ ተይዟል።

አቶ በድሉ ተመስገን ከተባለ ግለሰብ የ182 ሺህ 735 ብር ዋጋ ያላቸው የወንዶች የስፖርት ጫማ እና አብርሃም ደንቡ በተባለ ግለሰብ የ25 ሺህ 645 ብር ዋጋ ያላቸው የህፃናት ጫማ ጀማል በደዊ በሚል ስም የገዙበት ደረሰኝ ተገኝቷል።

ከፍርድ ቤት በተሰጠ የብርብራ ፈቃድ መጸዳጃ ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ ክፍሎች የህፃናትና የአዋቂዎች የስፖርት እንዲሁም ነጠላ ጫማዎች በካርቶን ታሽገው ተገኝተዋል።

የመጀመሪያው ግለሰብ በሁለት ክፍለ ከተሞች በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ገብሩ ኃይለማርያም በሚል ስም እንዲሁም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ጀማል በደዊ በሚል ስም መታወቂያ አውጥቶ ሲንቀሳቀስ የቆየ ነው።

ሁለተኛው ግለሰብ አቶ ሙጂብ መሐመድ መርካቶ አካባቢ በአሮጌ ጫማ መሸጫ ሱቅ ስም የንግድ ፈቃድ አውጥቶ ነገር ግን አዳዲስ ጫማዎችን አሮጌ በማስመሰል ያለ ህጋዊ ደረሰኝ ከወደብ እንደሚያስገባ ተረጋግጧል።

አዳዲስ ጫማዎችን አሮጌ በማስመሰል በህገ-ወጥ መንገድ ካስገባ በኋላ አጥቦ ለገበያ የሚያቀርብበት የጫማ ማጠቢያ ማሽን በቤቱ ተገኝቷል።

ግለሰቡ አሮጌ ጫማዎችን አስኮ ጨረታ ከተባለው አካባቢ ያለደረሰኝ እንደሚገዛ ቢናገርም ቤቱ ሲበረበር ግን አዳዲስ ቶርሽን ጫማዎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን  የኮልፌ ቀራኒዮ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህግ ማስከበር ምክትል ስራ አስኪያጅ ኮማንደር ደራራ ጫላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ያለ ደረሰኝ በግለሰቦቹ መኖሪያ ቤት ተከማችተው የነበሩ የተለያዩ ጫማዎች ከአካባቢው ኅብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ ተይዘዋል።

የጉምሩክን ስርዓት ያልተከተለ ዕቃ ሁሉ እንደ ኮንትሮባንድ ስለሚቆጠር ግለሰቦች የፈጸሙት ድርጊት ህገ-ወጥ ድርጊት መሆኑን ጠቁመዋል።

በቦታው ተገኝቶ ማረጋገጥ እንደተቻለው ከሁለቱም ቤቶች በተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው ጫማዎች በካርቶን ታሽገው በሚሸጥ መልክ ተደርድረዋል።

ቆጠራው ተከናውኖ በደብዳቤ ቃሊቲ ጉምሩክ እንደሚገባ የገለጹት ኮማንደር ደራራ “ቆጥረን እንደጨረስን ግምቱን እናሳውቃለን” ብለዋል።

ምርቶቹ የአገር ውስጥ ባለመሆናቸው የሚገቡበት መንገድ አገርን የሚጎዳና ህጋዊ ነጋዴውን ኪሳራ ላይ የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጊቱ ህዝብና መንግስትን የሚጎዳ የወንጀል ተግባር በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆንና ጥቆማ በመስጠት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን የመከላከል ስራዎችን እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ